ፕሬዝደንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ‘ከጠብ አጫሪነት ይልቅ በውስጥ ችግሮቿ ላይ ታተኩር’ ሲሉ ተናገሩ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/11/2017፡ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአገራቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ጎረቤታቸው ኢትዮጵያ ከምታሰማው የጠብ አጫሪነት ንግግር ተቆጥባ በአንገብጋቢ የውስጥ ችግሮቿ ላይ ታተኩር ሲሉ ተናገሩ።
ፕሬዝደንቱ ይህንን የተናገሩት ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም. ከአገራቸው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢው ጋር ባደረጉት ሁለተኛ ክፍል ቃለ ምልለሳቸው ነው።
ባለፈው ቅዳሜ በቀረበው ክፍል አንድ ላይ በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ውዝግብ አንስተው የነበረ ሲሆን፣ በሁለተኛው ክፍል በኤርትራ የውስጥ ጉዳዮች ያተኩራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሰፊ ሰዓት ሰጥተው ስለ ጎረቤት አገር ሱዳን እንዲሁም ስለ የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ እና ሌሎች ጉዳዮች ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ በዚሁ ንግግራቸው ኢትዮጵያን በመጥቀስ ጠብ አጫሪ ንግግሮችን ከመስማት ይልቅ አንገብጋቢ የውስጥ ችግሮቿን ለመፍታት ትኩረት እንድታደርግ በድጋሚ አሳሰበዋል።
ፕሬዝደንቱ በመጀመሪያው ክፍል ቃለ ምልልስ ላይም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የላከችውን ደብዳቤ ጠቅሰው “አስገራሚ የውሸት ክስ” በማለት ማጣጣላቸው ይታወሳል።
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅዳሜ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም. በሰጡት የመጀመሪያ ክፍል ቃለ ምልልስ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ መንግሥትን ከስሶ ለተባበሩት መንግሥታት ያስገባውን ደብዳቤ ‘ርካሽ ውሸት’ ሲሉ አጣጥለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ “የብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ለመሸፈን ያቀረበው ርካሽ ውሸት ነው” ብለው ነበር።
ትናንት ረቡዕ ምሽት በተላለፈው ሁለተኛው ክፍል ቃለ ምልልሳቸው ላይም “የአዲስ አበባው መንግሥት ሌሎች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉት፤ መስራት ከፈለገ።
ማስቀደም ያለበት ጉዳይ ትቶ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ገብቶ አለመረጋጋት የሚፈጥርበት ምክንያት ምንድን ነው? አያስፈልግም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ቀጠናው እያመሱ ያሉት እስራኤል፣ ኢሚሬትስ፣ ፈረንሳይና አሜሪካ በቀደም ተከተል መሆናቸው ያነሱት ኢሳያስ ኢትዮጵያም በሱዳን ግጭት እጅ እንዳለባት ጠቁሟል። የኢትዮጵያ መንግስት በኢሳያስ ክሶች ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።