ኢትዮጵያ
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የተለቀቀው መረጃ “ወደ ጠላት በኮበለለ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ” የተሰራጨ ነው ሲል አስተባበለ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/11/2017፡ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የተለቀቀው መረጃ “ወደ ጠላት በኮበለለ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ” የተሰራጨ ነው ሲል ገልጿል።
መግለጫው ተቋሙን እንደማይወክልም አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለት የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ በተሰራጨ መግለጫ፤ “የብልፅግና ቡድን የአፋር ህዝብ ልዑላዊ ግዛት ለታሪካዊ የአፋር ጠላት ለሆነው ለኢሳ አሸባሪዎች አሳልፎ ለመስጠት ተስማምተዋል” ሲል ከሷል።
አክሎም “የአፋር ህዝብ ጠላት ከሆነው ከህወሓት ቡድን ላፈነገጠው ለእነ ጌታቸው ረዳ ቡድን ማሰልጠኛና እስትራቴጂካዊ ቦታ በአፋር ልዑላዊ ግዛት ውስጥ መስጠታቸው ደርሰንበታል” ብሏል።
ይህን ተከትሎ፤ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፤ የፌስቡክ ፔጁን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚኒኬሽን ባለሙያ የነበሩት ሀጅ ጃሚኢ አደም አህመድ ይዘው “ወደ ጠላት ኮብልለዋል” ብሏል። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ “ጠላት” ሲል የጠራውን አካል በስም አልጠቀሰም። ፅሑፍ እስካሁን ከፌስቡክ ገፁ አለመነሳቱ አነጋጋሪ ሆኗል።