
ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/11/2017፡ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በማህበራዊ ትስስራቸው ባጋሩት ፅሑፍ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ቅዳሜ ዕለት ስለ ኢትዮጵያ ለሰጡት ቃለ ምልልስ “ግን በሰማንያ ዓመት አንድ አይነት ንግግር አይሰለችም?” በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
“ህገመንግስት፣ ምርጫ፣ ነፃ ፕሬስ፣ ህግ አውጭ፣ ..ወዘተ የሌለበት እና ይህን ለመፍቀድ ያልደፈረ ሰው በምን አንደበት ነው ታአምር የሚሠሩ ጀግኖችን የሚተቸዉ? በማለት የተቹት ሚኒስትሪ “ተፎካካሪን እያስወገዱ፣ፍፁማዊ ስልጣንን እየተቆጣጠሩ ፣ ግጭትና ከበባን እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙ፣ ብሔራዊ አገልግሎትን እንደ ባርነት እየተጠቀሙ ፣አምራቹ ሀገሩን ጥሎ እንዲሰደድ እያደረጉ፣ ጎረቤትን እየበጠበጡ እኛ ብቻ ቅዱስ ነን ማለት ይቻላልን? በማለት ፕሬዝዳንቱን ወርፏል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሰጡቶ ቃለ ምልልስ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የላከውን ደብዳቤ “አስገራሚ የውሸት ክስ” ሲሉ ማጣጣላቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንቱ ‘ይህ ርካሽ ውሸት ነው’ ሲሉ ያጣጣሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ “የብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ለመሸፈን ያቀረበው ርካሽ ውሸት ነው” ብለዋል።
በዚህ ሁለት ሰዓት በፈጀው ቃለ ምልልስ ላይ ፕሬዘዳንት ኢሳይያስ ስለ ኢትዮጵያ እና የወደብ ጉዳይ፣ ስለ ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን የኤርትራ እና የአሜሪካ ግንኙነት መሻሻል፣የጎረቤት አገራት እና ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።