ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ ዜጎችን በሞት እንደቀጣች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 01/11/2017: አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰኞ ዕለት ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሟን አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በውጪ ዜጎች ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አምነስቲ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ዓመት 345 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆን ይህም አምነስቲ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው ብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 2014 እስከ ሰኔ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ 1,816 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ የፕሬስ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ባለፉት አስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የሞት ቅጣት ከተቀበሉት 597 ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውንም ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ 2024 ሳዑዲ አረቢያ 345 የሞት ቅጣት ፈፅማለች።
ባለፉት ስድስት ወራት፣ ከጥር እስከ ሰኔ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ በድምሩ 180 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች።
በሰኔ 2025 ብቻ አገሪቱ 46 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆን 37ቱ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ነው።
ከእነዚህም መካከል 34ቱ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከናይጄሪያ፣ ከፓኪስታን፣ ከሶማሊያ እና ከሶሪያ የመጡ የውጭ አገር ዜጎች መሆናቸውን አምነስቲ ገልጿል።
በተለይ ባለፉት አስርት ዓመታት 155 ፓኪስታናዊ፣ 66 ሶሪያዊያን፣50 ዮርዳኖሳውያን፣39 የመናውያን፣ 33 ግብፃውያን፣ 32 ናይጄሪያውያን ፣ 22 ሶማሌያውያን እና 13 ኢትዮጵያውያን በሞት መቀጣታቸውን አምነስቲ ገልጿል።