
ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/1/2017፡ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲን ግብዣ ተከትሎ የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ግብጽ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በግብፅ የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነችው ኤል አላሜይን ሲደርሱ፣ በግብፅ ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
መሪዎቹ በሁለቱ ወንድማማች አገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር እና ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቪላ ሶማሊያ አስታውቋል።
በተጨማሪም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ከግብጹ አቻቸው ጋር በፀጥታ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና፣ በቀይ ባህር መስመር ልማት እንዲሁም ሽብርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በሚደረጉ የጋራ ጥረቶች ላይ እንደሚመክሩ የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከዚህ በፊት ነሐሴ 2024፣ ግብፅና ሶማሊያ የመከላከያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ከስምምነቱ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ የሶማሊያ ባለሥልጣናት “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በታህሳስ 2023 አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ካነሳ ወዲህ ትልቁ የጦር መሳሪያ ጭነት” ሲሉ የገለጹት የግብፅ ግዙፍ ወታደራዊ የጭነት መርከብ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ወደብ መድረሱ አይዘነጋም።
በሶማሊያ የግብፅ ወታደራዊ ተሳትፎ መጨመሩ ከኢትዮጵያ በኩል ትችት የገጠመው ሲሆን ኢትዮጵያ ድርጊቱን ካይሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ካላት ተቃውሞ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ትመለከተዋለች። ሰሙኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር እንደሚመረቅ መግለፃቸው ተከትሎ ግብፃዊያን መዛታቸው የሚታወስ ነው፡፡