
ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/1/2017፡ በኬንያ ዛሬ ሰኞ፣ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. ከታቀደው ተቃውሞ በፊት የአገሪቱ ፀጥታ ኃይሎች የዋና ከተማዋ ናይሮቢ ማዕከላዊ ክፍል መግቢያ እና መውጫ ሁሉንም ዋና መንገዶችን መዝጋቱን ቢቢሲ ዘግበዋል።
በዛሬው ዕለት የታቀደውን ተቃውሞ በመስጋት የንግድ ተቋማት ተዘግተው አብዛኛው የከተማዋ ማዕከል ወና እንደሆኑ መረጃው ጠቁመዋል።
በየመንገዶቹ የፀጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ቁጥር ሲሰማሩ፤ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች እንዳይመጡ ትዕዛዝ ተላልፎባቸዋል።
በከተማዋ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት እና የኬንያ ፓርላማን ጨምሮ ቁልፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚወስዱ መንገዶች በአደገኛ ሽቦ እንዲታጠሩም ታውቀዋል።
ፖሊስ ከተቃውሞው አስቀድሞ እሁድ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ፀጥታን በማስከበር የሰው ሕይወት እና ንብረት የመጠበቅ ህገ መንግሥታዊ ግዴታው እንደሆነ ገልጿል።
ዛሬ የተጠራው ሕዝባዊ ተቃውሞ “ሳባ ሳባ” በመባል የሚጠራውን በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በአገሪቱ የተደረገውን ትግል ለማስታወስ ነው።
ኬንያውያን የፋይናንስ ሕግ ረቂቅ መነሻ በማድረግ የአገሪቱን ፓርላማ ጭምር ጥሶ የገባውን ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመትን ለመዘከር ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. ሕዝባዊ ተቃውሞ አካሂደዋል።