
ኢትዮሞኒተር፡ 27/10/2017፡ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግስትን በጦርነት ቀስቃሽነት እና በግዛት ጥሰት ከሰዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ፊርማ የወጣው ደብዳቤው ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መናድ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገድ፣ የመገናኛ መስመሮችን በማስተጓጎል እና የኢትዮጵያን ግዛት እንደያዘች መቀጠሏን ይገልጻል።
የኤርትራ መንግስት በተደጋጋሚ የጦርነት ትንኮሳዎች እያደረገ መሆኑን ደብዳቤው ይከሳል።
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ ኤርትራ የጦርነት ፕሮፖጋንዳ ከፍታብኛለች በማለት ይወቅሳል። ስለ ኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሚቀርብበት ክስ ሲመልስ በአልጀረስ ስምምነት መሰረት የተሰጠኝ ቦታ ላይ ነኝ በማለት ያስተባብላል። ይልቁኑም ኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛቴን ለ20 ዓመታት ያክል ይዛብኝ ቆይታለች በማለት ተገልብጦ ሲከስ ይሰማል። ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኤርትራ ሰራዊት ከአልጀርስ ስምምነት ውጪ የትግራይ መሬት ይዞ አሰንደሚገኝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት ለፓርላማ በሰጡት ማብራርያ “የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኤርትራ አንድም ጥይት አይተኩስም” ማለታቸው ይታወሳል።