የህዳሴ ግድብ ክረምት ሲጠናቀቅ እንደሚመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ገለፁ።
ግብፅ፣ ሱዳንና ሌሎች የተፋሰስ አገሮች ህዳሴ ግድብን መጥቶ እንድያስመርቁም ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮሞኒተር፡ 26/10/2017፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ በፓርላማ ፊት ተገኝቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸወሰ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም ዘርፎች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራርያ የሰጡ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ ታላቁ ህዳሴ ግድብን የሚመለከት ነው።
ግድቡ ክረምት ጋብ ሲል እንደሚመረቅ የገለፁት ዶ/ር አብይ “ግብፅ፣ ሱዳን እና የተፋሰሱ ሀገራት መስከረም ወር ህዳሴን ስናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንድትሆኑ በምክር ቤቱ ስም ግብዣዬን አቀርባለው” ብሏል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጭው 2018 ዓ.ም መስከረም ወር እንደሚመረቅ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ህዳሴ ከመመረቁ በፊት እንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ ግን አይችሉም ፤ እናስመርቀዋለን” ብለዋል።
“ህዳሴ ግድቡ ለግብጽም ለሱዳንም በረከት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ግብፅ፣ ሱዳን እና የተፋሰሱ ሀገራት መስከረም ዝናቡ ጋብ ሲል ህዳሴን ስናስመርቅ የደስታችን ተካፋይ እንድትሆኑ በተከበረው ም/ቤት ስም ግብዣዬን አቀርብላችሗለሁ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ “የአስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ የቀነሰው የለም፤ አሁንም ግብጽም ሱዳንም እንዲጎዱ ፍላጎት የለንም” ሲሉም ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁንም ከግብጾች ጋር ለመስራትና ለመነጋገር ዝግጁ ናት ብለዋል።
የሰዎስቱም አገራት ድርድር በግብፅ እምቢተኝነት መቋረጡ ይታወሳል።