14 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ፡፡

ኢትዮሞኒተር፡ 24/1/2017፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የ14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል ተጠቆመ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለውጭ ሰብዓዊ እርዳታ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ መሰረዛቸውን ተከትሎ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል አንድ የሕክምና ሪፖርት ጠቁሟል። ካለ እድሜያቸው ሕይወታቸው ከሚያልፉት ሰዎች ውስጥ አንድ ሶስተኛ ያህል ሕፃናት መሆናቸውን የጥናቱ ግኝት አሳይቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው መጋቢት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የሚሰጡ 80 በመቶ መርሐ ግብሮችን መሰረዙን ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል። ከጥናቱ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ “ለበርካታ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ውጤቱ ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አሊያም ከግዙፍ ግጭት ጋር የሚነፃፀር ነው” ብለዋል።
የረድኤት ድጋፉ “ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተጋላጭ ሕዝቦች ጤና ላይ የታየው እድገት በአፋጣኝ እንዲገታ ወይም ወደነበረበት እንዲመለስ አደጋ ደቅኗል” ሲሉ በባርሴሎና ዓለም አቀፍ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ አክለው ተናግረዋል። ዘ ላንሴት ያወጣወ ሪፖርት የዓለም መሪዎች በስፔን ሲቪያ ከተማ በዚህ ሳምንት በመንግሥታቱ ድርጅት የተመራ እና ከአስር ዓመታት በኋላ ግዝፉ የሆነው ጉባኤ ከመካሄዱ አስቀድሞ ነው።
ከ133 አገራት የተገኘ መረጃን የተመለከተው የተመራማሪዎች ቡድን እ.አ.አ ከ2001 እስከ 2021 ድረስ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የUSAID ድጋፍ 91 ሚሊዮን ሰዎችን ከሞት የታደገ እንደነበር ተገልጿል። ተመራማሪዎች ከወራት በፊት በአሜሪካ መንግሥት ይፋ የተደረገው 83 በመቶ ድጋፍ መቀነስ የሞት ምጣኔን ከፍ እንደሚያደርግም ግመታቸውን አስቀምጠዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የእርዳታ መሰረዙ ሕይወታቸውን መታደግ እየተቻለ 14 ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ሞት ይመራል ብለዋል። ይህ አኃዝ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 4.5 ሚሊዮን ሕፃናትን ጨምሮ ሲሆን ይህም ማለት 700 ሺህ ሕፃናት በየዓመቱ ሕይወታቸው ያልፋል ማለት ነው።