በትግራይ ሙስሊም ሴቶች ፈተና እንዳይፈተኑ ተከለከሉ፡፡

ኢትዮሞኒተር፡ 24/1/2017፡ በአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች የ12ተኛ ክፍል ፈተናን እንዳይፈተኑ መደረጋቸው ተሰማ።
በትግራይ ክልልል ማእከላዊ ዞን አክሱም ከተማ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሂጃብ ጋር በተያያዘ ሳይፈተኑ መቅረታቸው መረጃዎች ጠቁሟል ፡፡ ተማሪዎቹ ከዚህ በፊት በሂጃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ለ8 ወራት ያህል ከትምህርት ተገልለው የቆዩትን እነዚህን ተማሪዎች በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የ12ተኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናን እንዲፈተኑ ፎርም ማስሞላቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ትላንትና በተጀመረው የ12ኛ ክፍል ፈተና እነዚህ ተማሪዎች እንዳይፈተኑ ተደርገዋል መባሉ ተሰምቷል፡፡ ሆኖም የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃውን ከእውነት የራቀ ብሎታል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት የእነዚህ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች አድሚሽን ካርድ ዘግይቶ የደረሰው ቢሆንም ትላንት እንዲፈተኑ ሁኔታዎች ተመቻችቶ ነበር ብለዋል። አሁንም ቢሆን በሁለተኛው ዙር እንዲፈተኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ ይህንን የሚገልፅ ሀሳብ በትግርኛ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ ፅፈዋል፡
በመጪው ሀሙስ በሚጀመረው ሁለተኛ ዙር ፈተና ላይ እነዚህን ተማሪዎች ለማስፈተን ጥረት እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአክሱም ከተማ ከዚህ ቀደም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሂጃብ ጋር በተያያዘ ምክንያት የ8ተኛ ክፍል ፈተናን ሳይፈተኑ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡