
ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/1/2017፡ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተሰኘው ተቋም በአዲስ አበባ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው እስር እንዲቆም አሳሰቧል፡፡
ተቋሙ ትላንት ሰኔ 23 ባወጣው መግለጫ በመንግስት አካላት በተለይም በአዲስ አበባ ፖሊስ የትግራይ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ እስርና እንግልት እየደረሰ መሆኑን ገልፆ ይህ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም ከሰኔ 14 ጀምሮ ከእስር ከተፈቱ፣ ከእስረኞች ቤተሰቦችና እስሩን ከሚፈፅሙ የፖሊስ አባላት አነጋግሬ አገኘሁት ያለው የምርመራ ውጤት ይፋ አድርጓል።
በውጤቱ መሰረትም በተለያዩ የአዲስ አበባ አከባቢዎች የትግራይ ወጣቶች በማንነታቸው ምክንያት ከመንገድ እየታፈሱ እየታሰሩ ነው። በየካቲት ወር ተመሳሳይ ክስተት እንደነበረ ያስታወሰው ድርጅቱ ቢሆንም ያኔ ድርጊቱ እንዲቆም በደብዳቤ በማሳወቁ እስሪ ጋብ ብሎ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ ሁኔታው በሰኔ ወር አገርሽቶ በርካታ የትግራይና የኤርትራ ወጣቶች እየታሰሩ ነው ብለዋል።
የሚታሰሩ ሰዎች ለሳምንታት ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በጠባብ ክፍል ታስሮ እንደሚገኙም አስረድቷል። ከሳምንታት እስር በኃላ የወጡ ወጣቶች ለድርጅቱ እንዳስታወቁት የሚታሰሩበት ምክንያት ሲጠይቁ “ከላይ የወረደ መመሪያ ነው” የሚል ምላሽ ከፖሊሶች እንደሚሰጣቸው ገልጿል።
የታሰሩት እንዲፈቱ፣ በወንጀል የሚያስጠረጥራቸው ጉዳይ ካለም በህጉ መሰረት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ያሳሰበው ድርጅቱ ጨምሮም ‹‹የዘፈቀደ እስር በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲከናወን የወሰኑ፣ ትእዛዝ የሰጡና እየፈፀሙ ያሉ አካላት ውሳኔያቸውና ተግባራቸውን በመመርመር በህግ ተጠያቂ እንደሆኑም›› ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት ተቋም ጠይቋል፡፡