አፍሪካኢትዮጵያ

ቋፍ ላይ ያለው ግንኙነት!

ኢትዮ ኤርትራ ዳግም ወደ ጦርነት?

 ኢትዮ ሞኒተር፡ 23/10/2017፡ ኢትዮ ሞኒተር ትንታኔ

ከሁለት አስርት ዓመታት በኃላ በ2010 መጨረሻ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ብዙም ሳይቆይ እንደገና መሻከሩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድረዋል፡፡ በርግጥ ብዙዎች የሁለቱም አገሮች ግንኙነት በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲያዊ መርህ ላይ የተመሰረተ ነበርን? ብሎ እንዲጠይቁም ተገዷዋል፡፡ የትግራይን ጦርነት በጋራ ለመጀመር የተካሄደ መርህ አልባ  ግንኙነት እንደነበረ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡ ግንኙነቱ የሁለቱም አገሮችና ህዝቦች ጥቅም መሰረት ያደረገ ሳይሆን በመሪዎቹ ላይ የተንጠለጠለ ስለነበረ ነው አሁን ወደዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በማለት የሚከሱም አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከኤርትራ ስርዓት ባህሪ አንፃር ይህ የሚጠበቅ ነው ብሎ ይሞጉታሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት አሁን አደገኛ ወደ ሆነ ደረጃ እንደደረሰ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የሁለቱም አገሮች እንካሰላንቲያ ወዴት ሊያመራ ይችላል? በርግጥ ሁለቱም አገሮች ወደ ጦርነት ለመግባት የሚያስችላቸው በቂ ምክንያቶች አሉዋቸውን? ከሁለቱም አገሮች አልፎ በቀጠናው ሊኖረው የሚችል እንድምታስ ምንድነው? ኢትዮ ሞኒተር እነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች በትንታኔ ይዳስሳቸዋል፡፡

የሁለቱም አገሮች ግንኙነት እየቀዘቀዘ የመጣው ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኃላ ቢሆንም ይበልጥ መካረር የጀመረው ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ነሐሴ 2016 ዓ/ም ስለባህር በር አጀንዳ ካነሱ በኃላ ነው፡፡ ከዚህ ግዜ ጀምሮ የሁለቱም አገራት ሚድያዎች እና የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች አንዱ ሌላኛውን የሚያጠቁ መረጃዎች እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ጊዝያት ደግሞ ወደ መሪዎች ደረጃ ተሸጋግሮ እረስበርሳቸው ሲወነጃጅሉ ይታያል፡፡ አሁን ደግሞ በመንግስት ደረጃ መግለጫዎች እስከ መስጠት ተደርሰዋል፡፡ ሰሙኑን የኤርትራ መንግስት ያወጣው መግለጫ እንደሚመለክተው ኢትዮጵያ ጦርነት ለመጀመር ሰበብ እየፈለገች ነው የሚል ነው፡፡ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ “ግጭት ለመቀስቀስ እና ምክንያታዊ ለማስመሰል” ዲፕሎማሲ መልዕክቶችን እየተጠቀመች ነው ሲል ነው የከሰሰው፡፡ የኤርትራ መንግስት ይህን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ መንግስት ጻፈው በተባለው ደብዳቤ መነሻነት ነው፡፡ የኤርትራ መንግስት “በኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ በመፈጸም “ እና “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን እየጣሰ ነው” የሚል ክስ የኢትዮጵያ መንግስት  ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ እና ለበርካታ ሀገራት መንግስታት ዲፕሎማሲያዊ መልዕክቶችን ልከዋል በማለት ይከሳል፡፡ ይህም “ግጭት ለመቀስቀስ እና ምክንያታዊ ለማስመሰል የሚደረግ ጥረት አካል ነው” በማለት ወቅሰዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰኔ 19 ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “እያየለ በመጣው የጦርነት አጀንዳው ላይ ድጋፍ ለማግኘት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን ባለፉት ቀናት “የዲፕሎማሲያዊ ዘመቻዎችን አጠናክሯል” ይላል፡፡

ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ “አላስፈላጊ መግለጫ በማውጣት” እና  “ወታደራዊ ማስፈራሪያ በመፈጸም ” ላይ ይገኛል ሲል የገለፀው የኤርትራ መንግስት፤ እነዚህ እርምጃዎች የኤርትራ ወደቦችን “ከተቻለ በህጋዊ መንገድ ካልሆነም በወታደራዊ ኃይል” ለመያዝ የሚያደረገው “ሰፊ ስትራቴጂ ጥረት አካል ናቸው” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት “በርካታ የጦር መሳሪያ ግዥዎችን ” እና “መንግስትን የማዳከም በርካታ ጥረቶችን” እያደረገ እንደሚገኝም መግለጫው ጠቅሰዋል። የኤርትራ መንግስት “መንግስትን የማዳከም በርካታ ጥረቶችን” ያለው ምን እንደሆነ በግልጽ ባገልጽም የኢትዮጵያ መንግስት ብርጌድ ንሃመዱ የሚባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ይደግፋል በሚል እንደሚታማ ይታወቃል፡፡

ይህ የኤርትራ መግለጫ የተሰጠው፤ ትክክለኛነቱ ያለተረጋገጠ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ነው። ከኢፌድሪ ውጭ ጉዳይ ሚስቴር እንደወጣው የሚያመለክተው ደብዳቤው “የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ትንኮሳዎች መፈጽሙን “ እና “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ጥሷል” የሚል ክስ የያዘ ነው። እነዚህ ድርጊቶች “የዓለም አቀፍ ህግን በግልፅ የሚጥሱ” እና “የአፍሪካ ቀንድን ደካማ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ የበለጠ ያባብሳሉ” ይላል ደብዳቤው።

በተጨማሪም ኤርትራ “የግዛት ወረራ እያካሄደች”፣ “በሲቪሎች ላይ ጥቃት እየፈጸመች” እና “ለተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ድጋፍ እያደረገች ነው” ሲልም ይከሳል። ደብዳቤው ኤርትራ የምትደግፋቸው የታጠቁ ቡድኖች እነማን መሆናቸው ባይጠቅስም ኤርትራ የአማራው ፋኖ ታጣቂ ሐይል ትደግፋለች በማለት እንደምታማ ይታወቃል፡፡ ይህ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጽፎ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደተላከ የሚያሳየው ደብዳበ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ በምታካሂደውን የጦርነት እንቅስቃሴ ” አጋሮቿን  መጠቀሟን እንድታቆም” የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስቁማት የሚጠይቅ ነው። ይህን ተከትሎ ነው የኤርትራ መንግስት ይህ ጥሪ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው በማለት የኢትዮጵያ መንግስትን እየከሰሰ ይሚገኘው፡፡ ኢትዮጵያ መንግስት ግን ስለደብዳበው እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ “ሉዓላዊ” የተባለ ለመንግሥት ቅርበት ያለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞትዮስ የኤርትራ መንግሥትን በተመለከተ “ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደብዳቤ ማሠራጨቱን” ዘግቦ እንደነበር የሚታወስ ነው። ደብዳቤው ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚያመለክት ሲሆን፣ “የሰሜን ኢትዯጵያን ጦርነት ኢትዮጵያን ለማዳከም እንደ ዕድል ተመልክቶት የነበረው” የኤርትራ መንግሥት፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠበኛ አቋም መያዝ ጀመረ” ሲል ይጠቅሳል። የኤርትራ መንግሥት ግን ይህ “የተለመደ ማደናገሪያ” ሲል ጠርቶታል።

የኤርትራ መንግሥት መግለጫ የወጣው በአዲስ አበባ እና አሥመራ ባለሥልጣናት አንዳቸው ሌላኛቸውን ዒላማ ያደረጉ ንግግሮችን እያሰሙ ባሉበት በዚህ ወቅት መሆኑ ነገሩ ይበልጥ ያወሳስበዋል እየተባለ ነው። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ግንቦት በተከበረው የሀገሪቱ 34ተኛ የነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በገዢው ብልፅግና ፓርቲን ላይ በግልጽ ውንጀላዎችን አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ነው።ኢሳያስ በዚያን ወቅት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት “የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም” የጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ይህን ተከትሎ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፤ “አገር ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ” አገራት “በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር መሞከራቸው የተለመደ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን” ብለው ነበር። ለዚህም ምላሽ የሚመስል መልዕክት ያጋሩት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል “በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ደጋፊዎች ስለ ኤርትራ ማንኛውንም ነገር መተቸት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል” ነበር ያሉት።

በግንቦት መጨረሻ ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ ግን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር “የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገባም” ሲሉ ማስተባበላቸው የሚታወስ ነው። ዶ/ር ጌድዮን እንዲህ ቢሉም ውንጀላዎቹ ግን በሁለቱም ወገኖች አልቆሙም፡፡ የህዝብ ተወካዮች አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‘ሆርን ሪቪው’ በተባለ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ፅሑፍ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲያስወጣ ጠይቀዋል፡፡ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር የተሰለፈው የኤርትራ ጦር አሁንም በትግራይ መሬት እንደሚገኝ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የገለፁት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የኤርትራ ሰራዊትን ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጡ የጠየቁት በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የነበሩት ዲና ሙፍቲን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግን የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ እየተሳተፉ ነው መባላቸውን “መሠረተ ቢስ” በማለት ሲያጣጥሉ መቆየታቸው አይዘነጋም። ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ ሠራዊት በሕግ የተሰጠው ቦታ ላይ እንደሚገኝ እና ከዚያ ውጪ ያዛቸው ቦታዎች ካሉ የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረው ነበር። አምባሳደር ዲና ግን በጽሑፋቸው የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ታጣቂዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ ጭምር ነው የጠቀሱት፡፡ ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን እንዲያስቁመው ጥሪ አቅረበዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚለውን ጥያቄ የብዙዎች ሆነዋል፡፡

በቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተጽፎ በአልጄዚራ የሚድያ አውታር የተሰራጨው ፅሑፍ እንደሚያመልከተው የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመጀመር በቂ ዝግጅት እያደረገ እንሆነ ነው፡፡ የኤርትራ የጦረኝነት ባህሪ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ ጠንቅ እንደሆነ የሚገልጸው የዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ፅሑፍ ይህን አደገኛ ኣካሄድ የዓለም ማህበረሰብ ዝም ብሎ ሊመለከተው እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቀጠናው ለሚፈጠር ነገር ተጠያቂ የሚያደርገውን የዶ/ር ሙላቱን ጽሑፍ ተከትሎ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል፣ “ኢትዮጵያ ኤርትራን እየተነኮሰች ነው” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው መልስ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ጄነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤም ተመሳሳይ ጽሑፍ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ጄነራል ፃድቃን በጽሑፋቸው “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በማንኛውም ቅፅበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ነበር ያሉት፡፡ “ጦርነቱ ሲያከትምም አሁን የምናውቀው የአገራቱ ጂኦግራፊ ይለወጣል። በአፍሪካ ቀንድና ከቀይ ባሕር አሻግሮም ጉልህ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ያስከትላል” ብለው ነበር። ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚቀሰቀሰው ጦርነት የሱዳንና የቀይ ባሕር ደኅንነት ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ገልፀዋል። ጄኔራል ፃድቃን ከፕሪቶርያ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠልሸቱን በማስታወስ ጦርነት “አይቀሬ” መሆኑንም ጠቅሰዋል። “ዝግጅቱ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው። ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት አንዳች ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደኋላ መመለስ ይከብዳል” ብለው ነበር።

በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ የግጭቶች አማካሪ ፕሮፌሰር ሸትል ትሮንቮል እንደሚሉት በአፍሪካ ቀንድ የጦር ጥምረቶች በፍጥነት እየተቀያየረ ነው፡፡ “የግብፅ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ጥምረት ለኢትዮጵያ አደጋ ነው፤ ሆኖም ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጦርነት የመክፈት ተጨባጭ ምክንያት አላት” ይላሉ፡፡ ይህም የኤርትራ ሰራዊት ይዞት ከሚገኝ የትግራይ መሬት ካልወጣ በሁለቱ አገራት ጦርነት ሊነሳ ይችላል በማለት ይገልፃሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን የኤርትራ መንግስት ሰራዊቱ ከትግራይ ግዛት ማውጣት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

የምስራቅና ደቡብ ኣፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ እና ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት ” የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳይ ያበቃለት ነው”  ይላል፡፡ ምልክቶቹ ወደዚህ ድምዳሜ እንድትደርስ የሚያስገደዱ እንደሆኑም ይገልፃል፡፡ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት ከቃላት ፕሮፖጋንዳ አልፎ ወደ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መሸጋገራቸውም ይጠቁማል፡፡ የኤርትራ መንግስት በዓሰብ፣ ባድመ እና ኦሞሐጀር አከባቢዎች ሰራዊቱ የማስፈር ሰፊ ስራ መስራቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ በዓፋር አካቢ በርካታ ሰራዊት እና የጦር መሳሪያዎች ማስጠጋቱ ማርቲን ፕላውት ዘግበዋል፡፡ ትኩረቱን በአፍሪካ እና ኤስያ አድርጎ my view on News በሚል የሚዘግበው ህንዳዊው ሳጂድ በርግጥ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ? በማለት ይጠይቃል፡፡ ሁለቱም አገሮች በትግራዩ የሁለት ዓመታት ጦርነት በወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም የተዳከሙ አገሮች እንደሆኑ የሚጠቅሰው ሳጂድ በህዝባቸው ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትም ቀንሰዋል ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኤርትራ ወጣት ማቆሚያ በሌለው ብሄራዊ አገልግሎት ከአገሩ ፈልሶ አልቀዋል፤ በኢትዮጵያ ለ7 ዓመታት የቀጠለውን የእርስ በርስ ጦርነት እና አሁን አጋጥሞ ያለው የኑሮ ውድነት ህዝቡ እንዳሰለቸውም ይጠቁማል፡፡ ስለሆነም ሁለቱም አገሮች ህዝብ አነሳስቶ ወደ ጦርነት ለመግባት እንደሚዳግታቸው ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ሁለቱም መንግስታት በቂ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆኑ ግን ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ለአምስት ዓመታት ብቻ የዘለቀው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት አሁን ካለው ፕሮፖጋንዳዊ ጦርነት አልፎ ወደለየለት የብረት ጦርነት እንዳይሸጋገር የሚሰጉት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ሁለቱም አገሮች በመስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆናቸው ደግሞ ጦርነቱ በሁለቱም አገሮች ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ የተለያዩ አገሮች ጭምር ሊሳተፉበት እንደሚችሉ የአፍሪካ ድህነነት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከግብፅ እስከ ሶማሊያ፣ከኢሚሬትስ እስከ ሳውዲ ዓረቢያና አሜሪካ በቀይ ባህር ዙሪያ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጦርነቱ በሁለቱም አገራት ፍላጎት ብቻ ላይወሰን ይችላል የሚባለው፡፡ ያም ሆነ ይህ የሰላምን አማራጭ ከማንኛውም በላይ የተሻለ አትራፊ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates