
ኢትዮሞኒተር፡ 19/10/2017፡ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ ከፍተኛ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግበዋል።
ዶ/ሩ በባህር ዳር ከተማ 13ኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልፀዋል። ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሊወስዱ እንደሚችሉ መረጃው አክለዋል።
ዶ/ር ዳንኤል በቁጥጥር ስር የዋሉት የጤና ባለሙያዎች የተሻሻለ ክፍያ፣ የተሻለ የስራ ሁኔታ እና ሌሎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለስላቸው ከግንቦት 4 ጀምሮ ሀገራ አቀፍ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ መቀስቀሳቸውን ተከትሎ ነው።
ዶ/ር ዳንኤል በጤና ባለሙያዎች እና በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውን “ዶ/ር ደቦል” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅን በመጠቀም በጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ ላይ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ እንደነበር ተገልጻል።
ሰሙኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የጤና ባለሙያዎች ተወካዮች ባነጋገሩበት ወቅት የባለሞያዎቹ ጥያቄ “በፖለቲካ ነጋዴዎች ተጠልፏል፤ እና ጉዳዩ ከእንግዲህ በእጃችሁ አይደለም” ካሉ በኃላ ነው።
ከስራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ ዶ/ር ማህሌት ጉኡሽ እና የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮናታን ዳኛውን ጨምሮ 47 ባለሙያውች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወቃል። እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ላደረጉት ስራ የማቆም አድማ ድጋፉን የገለፀው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር በቅርቡ መታገዱ ይታወሳል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር “ከግንቦት ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የጤና ሰራተኞች ስለ ህይወታቸው እና ደህንነታቸው ያነሱትን ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ አፋኝ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል” በማለት ከሰዋል።