ማህበራዊ

“አትሌት ገለቴ ቡርቃ ወደ ሚድያ በመውጣት ችግሯን ተናገረች እንጂ ይህ የበርካታ አትሌቶች ችግር ነው!” ሲል ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ተናገረ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 03/10/17፡  “አትሌት ገለቴ ቡርቃ ወደ ሚድያ በመውጣት ችግሯን ተናገረች እንጂ ይህ የበርካታ አትሌቶች ችግር ነው!” ሲል ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ተናገረ።

በሌላ በኩል “አትሌት ገለቴ የደረሰባትን በደል ግማሹን እንኳን አላወራችም” ስትል አትሌት መሰረት ደፋር ተናገረች።

ሰሙኑን የእውቅዋ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ህይወት ታሪክ ኣነጋጋሪ ሆኗል።
አትሌት ገለቴ በሚድያ ወጥታ እንደተናገረችው ከልጅነቷ ጀምራ ያፈረችውን ሃብቷ በባሏ መነጠቋ አስታውቃለች። ይህ ዓለም ያዘነበት ታሪክ ተከትሎ የኢ/ያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም አትሌት ገለቴ ቡርቃ ወደ ሚድያ በመውጣት ችግሯን ተናገረች እንጂ በጣም ብዙ አትሌቶች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፤ ወደፊትም እንዳይኖሩ መስራት ይጠበቅብናል ሲል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ተናግሯል፡፡

“የኢትዮጵያ አትሌቶች ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ እና የተሳካ ትዳር ያላቸው እንዳሉት ሁሉ፤ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እና መጥፎ ኑሮ የሚመሩ በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚገኙት አሉ” ያለው ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፤ ፌዴሬሽኑ ከአትሌት ገለቴም ሆነ “ሚዲያ ካላወቃቸው ሌሎች ገለቴዎች ጎን ለመቆም” ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

“እንደ ፌደሬሽን ከገለቴ ጎን መቆማችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሳወቅ እንወዳለን።” ያለ ሲሆን፤ የተበደሉትን ለማስካስ እና ወደፊትም እንዲህ አይነት ነገሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ
አሁን ላይ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን አትሌቶችን ከአደጋ የሚከላከል ኢንስቲትዩት መቋቋሙን አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት መሰረት ደፋር በበኩሏ፤ በሀገራችን ድምፃቸው ያልተሠማ ግን በደል የደረሰባቸው፣ ክህደት እና ጥቃት የተፈፀመባቸው “ብዙ ገለቴዎች አሉ” ብላለች።

“ገለቴ የደረሰባትን በደል ግማሹን እንኳን አላወራችም” ያለችው አትሌት መሰረት፤ “ገለቴ ከኛ ባልተናነሰ ሀገሯን ማስጠራቷን ማንም ሊደብቀው አይችልም” ስትል ተናግራለች።

“የገለቴን ታሪክ በቅርበት ስለማውቀው ግማሹን እንኳን ስለበደሏ አውርታለች ብዬ አላስብም። እኔን የሚያመኝ የገለቴ ንብረት ማጣት አይደለም። ግን ሁሌም ማዝነው ገለቴ አንድ ልጅ እንኳን የላትም ለመውለድ እንደምትፈልግም አውቃለሁ፤ ነገር ግን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የገጠማትን ችግር ለመፍታት በፍርድ ቤት ስትመላለስ ነው ያሳለፈችው” ስትልም የጉዳቷን አስከፊነት ገልጻለች፡፡

በመግለጫው አትሌቶችን ተወዳዳሪ እና ተሸላሚ ከማድረግ ባሻገር ሙሉ ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ የተመላከተ ሲሆን፤ “ይህም የፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን የመላውን ማህበረሰብ ትብብርና ኃላፊነት ጭምር የሚፈልግ ነው” ተብሏል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates