
ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/10/17፡-የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሎስ አንጄለስ ለተቃውሞ የወጡ ስደተኞች የፈጠሩትን አለመረጋጋት ለመቆጣጣር 2000 ወታደሮችን አሰማርተዋል። የካሊፎርኒያ አስተዳዳር የፌደራል የጸጥታ አካላት መሰማራትን ተቃውሞታል። “የካሊፎርኒያ ብሔራዊ ዘብ ስራን በመውሰድ 2000 ወታደሮች ማሰማራት ሆን ተብሎ ጠብ አጫሪነት ነው” “ውጥረትን ያባብሳል” ሲል አስተዳደሩ ተቃውመዋል።
ትራምፕ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንዲያባርሩ በዋናነት የሚደግፉት ቶም ሆርማን ቅዳሜ ዕለት ለፎክስ ኒውስ “ሎስ አንጀለስን ደህንንቷ የተጠበቀች እናደርጋታለን” ብለዋል። ቅዳሜ ዕለት በሎስ አንጀለስ ከፍተኛ የደቡብ አሜሪካ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ተቃውሞ ሠልፈኞቹ ከፌደራል የስደተኞች እና የጉሙሩክ ፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።
በፓራማውንት ዲስትሪክት ተቃውሞ ሠልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ እና ዱላ ጥቅም ላይ አውሏል።
ተቃውሞው እሁድም የቀጠለ ሲሆን ሰልፎች 4 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት በሎስ አንጀለስ ከተማ በበርካታ የመሀል ከተማ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የ12 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል አዋጅ ማፅደቃቸው ይታወሳል።
የአፍጋኒስታን፣ ምያንማር፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን ዜጎች ከአሜሪካ ታግደዋል።
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱ የ12 አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ የሚከለክለው አዋጅ ከዛሬ ሰኔ 2 ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።
እንዲሁም አዋጁ ከቡሩንዲ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቴርክሜኒስታን እና ቬንዙዌላ በመጡ ከዩኤስ ውጭ ባሉ እና ትክክለኛ ቪዛ በሌላቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ገደቦችን ይጥላል።
ባለፈው አርብ ለሁሉም የአሜሪካ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች በወጣው መመሪያ መሰረት አዲሱ እገዳ ከዚህ ቀደም በዝርዝሩ ውስጥ ካሉ ሀገራት ለመጡ ሰዎች የተሰጠውን ቪዛ አይሰርዝም። ነገር ግን፣ ከእገዳ ነፃ ለመውጣት ጠባብ መመዘኛዎችን ካላሟላ በስተቀር፣ ማመልከቻው ከሰኞ ጀምሮ ውድቅ ይሆናል። ከዚህ ቀደም ቪዛ የነበራቸው ተጓዦች እገዳው ተግባራዊ ከሆነ በኋላም ወደ አሜሪካ መግባት መቻል አለባቸው።
ከተዘረዘሩት አገሮች ውስጥ ብዙዎቹ ጥቂት ሰዎችን ወደ አሜሪካ የሚልኩት ቢሆንም፣ ሄይቲ፣ ኩባ እና ቬንዙዌላ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዋነኛ የስደተኞች ምንጭ ነበሩ።