
ኢትዮ ሞኒተር
አዲስ አበባ 27/09/2017 :ወደፊት ለሚቋቋመው “የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ”፤ ከመንግስት እና ከግል ተቋማት ሰራተኞች ደመወዝ መዋጮ እንዲሰበሰብ የሚያስገድደው የአዋጅ ድንጋጌ ተሰርዟል ተብሏል። ድንጋጌው በዛሬው ዕለት በፓርላማ ከጸደቀው “የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አዋጅ” ውስጥ እንዲወጣ የተደረገው፤ በሰራተኞች ላይ “ተደራራቢ ጫና እንዳያስከትል” ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ይኸው አዋጅ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከሚሰጧቸው 15 አይነት አገልግሎቶች “ለአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ” ገቢ እንዲሰበሰቡ የሚያስገድድ ድንጋጌ በውስጡ ይዞ ነበር። ፈንዱ “ለአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም” ተግባራት የሚውል እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
በገቢ ምንጭነት በአዋጁ ተዘርዝረው ከነበሩት መካከል “የመንግስት እና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኞች ከሚከፈላቸው የተጣራ ደመወዝ ላይ” መዋጮ እንዲሰበሰብ የሚያስገድደው ድንጋጌ አንዱ ነበር። አዋጁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት፤ ከደመወዝ ላይም ሆነ ከተለያዩ አገልግሎቶች ለፈንዱ ገቢ የሚሆን ገንዘብ መሰብሰብ “የግለሰቦችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል። በመሆኑም አዋጁ ተቃውሞ ስለገጠመው እንዲቀር መደረጉ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።