
ኢትዮ ሞኒተር
አዲስ አበባ 27/09/2017 : የ2018 የፌዴራል መንግሥት በጀት ወደ ሁለት ትሪልየን ብር የሚጠጋ ሆኖ እንዲጸድቅ ለውሳኔ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱ ተሰማ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ግንቦት 28 ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ፤ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ በጀት እንዲጸድቅ ለውሳኔ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል፡፡
ምክር ቤቱ የ2018 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥት በጀት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ በተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳት አንጻር መዘጋጀቱን ተገልጿል፡፡
የ2018-2022 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ እና የ2017 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን በመገምገም ተዘጋጅቶ የቀረበ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረትም ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ መቅረቡን ተገልጿል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ፤ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተመላክቷል፡፡