
ኢትዮ ሞኒተር
አዲስ አበባ 27/09/2017 : የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ የ12 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አገዷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ሶስት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳንን ጨምሮ የ12 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ ምንም አይነት ጉዞ እንዳያደርጉ መከልከላቸው ተገለጿል ሌሎቹ ሀገራት ቻድ፣ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ የመን፣ ሀይቲ፣ ኢራን፣ ማይነማር እና አፍጋኒስታን ናቸው።
የጉዞ ክልከላው ሙሉ በሙሉ ነው የተባለ ሲሆን ክልከላ የተላለፈባቸው ሀገራት ዜጎች ለቢዝነስ፣ ለጉብኝት፣ ዘመድ አዝማድ ለመጠየቅ፣ ለትምህርት እና በተለያዩ የአሜሪካ ቪዛዎች ወደ አሜሪካ ምድር መግባት አይችሉም ተብሏል፡፡
ክልከላ የተላለፈባቸው ሀገራት ዜጎች በማንኛውም በረራ ወደ አሜሪካ ምድር መግባት አይችሉም የተባለ ሲሆን ድንገት እንኳ ገብተው ከተገኙ በኤርፖርቶች ላይ ተይዘው እንዲቆዩ ይደረጋል መባሉም ተመላክቷል።
ሙሉ በሙሉ ክልከላ ተደርጎባቸዋል ከተባሉት ሀገራት በተጨማሪ የሰባት ሀገራት ዜጎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እና በከፊል ክልከላ እንዲደረግባቸው ፕሬዝዳንት ትራንፕ መመሪያ ማስተላለፋቸውን አለምአቀፍ መገናኛብዙሃን በዘገቧል።
ትዕዛዙ ተግባራዊ የሚደረገው ከመጪው ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን ከዚያ በፊት ቪዛ የተሰጣቸው የነዚህ 12 ሀገራት ዜጎች ምንም አይነት ክልከላ እንደማይደረግባቸው ተጠቁሟል።
ፕሬዝዳንት ትራንፕ ክልከላውን ያስተላለፍኩት “የአሜሪካን እና የህዝቦቿን ብሄራዊ ደህንነት እና ብሄራዊ ጥቅም ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ስላለብኝ ነው ማለታቸውንም ዘገባዎቹ አመልክቷል።
ዶናልድ ትራንፕ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ሙስሊም ማህበረሰብ ከሚበዛባቸው ሰባት ሀገራት ላይም ተመሳሳይ የጉዞ ክልከላ ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ውሳኔውን ተከትሎ
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እገዳውን ተችቷል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እገዳውን “አድሎአዊ፣ ዘረኛ እና ጨካኝ” ሲል ገልፆታል።