
ኢትዮ ሞኒተር
አዲስ አበባ 27/09/2017 : በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአሜሪካ መንግስት ይደግፋል አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸው÷ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት እና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች እንደምትገኝ አንስተው÷ ይህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚቀጥልም ትንበያ መኖሩን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ህልም ለማሳካት የባህር በር አማራጯን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት የሚደግፈው መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናው ወደ መረጋጋትና ሰላም እንዲመለስ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመልክተው÷ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ጠንካራ አቋም መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ግዙፍ ብቻ ሳትሆን አቅም እና ተጽዕኖ ያላት ሀገር ነች ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ÷ በቀጣናው መረጋጋትና ሰላም ለማስፈን ሀገራቱ በጋራ እንደሚሰሩም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።