መካከለኛ ምስራቅ

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ መከናወን የሚጀምር ታወቀ፡፡

የሚተካቸውም አዲስ መሪም ግብአተ መሪታቸውን ተከትሎ ይፋ እንደሚደረግ የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/06/2018፡- ምርጫውን የሚያከናውነው ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሲዘገብ፤ እስራኤልም ለደኅንነቷ ስጋት ሆኖ የሚቀጥል መሪ ከተመረጠ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች።

የጠቅላይ መሪው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሦስት ቀናትን እንደሚወስድ እና ከቀብሩ በኋላ የእስላማዊ ሪፐብሊኩ መሪ የሚሰይሙት መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ያላቸው መሪዎች በአካል ተሰብስበው ምርጫውን እንደሚያከናውኑ ፋርስ የተባለው የዜና ወኪል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ምርጫውን የሚያካሂደው ምክር ቤት አባላት ለአሜሪካ እና እስራኤል እንዳይጋለጡ “አስፈላጊ የሆነው የደኅንነት ጥበቃ እርምጃዎች በከፍተኛ ደረጃ መወሰዱን” ዘገባዎች እየጠቆሙ ነው።

ነገር ግን ‘ቆም’ በምትባለው ከተማ የሚገኘው የከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ጉባዔ አባላት ጽህፈት ቤት ማክሰኞ እንዲሁም ቴህራን ውስጥ ስብሰባ የሚያደርጉበት ቦታ ዛሬ በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቃት እንደተፈጸመበት ቢቢሲ ፐርሺያ ዘግቧል።

የአያቶላህ ኻሜኒ ቀብር በትክክል የት እንደሚካሄድ እስካሁን ያልተገለጸ ሲሆን፣ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ግን ማሻድ በምትባለው ከተማ ውስጥ በሚገኘው ስምንተኛው የሺዓ ኢማም የእምነት ስፍራ ሊሆን እንደሚችል እየዘገቡ ነው።

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሦስተኛው ጠቅላይ መሪ ማን እንደሚሆን እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኒው ዮርክ ታይምስ የኢራን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ የሟቹ መሪ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ አዲሱ መሪ እንዲሆን ከስምምነት ላይ መደረሱን እና ይፋ እንደሚደረግ የዘገበው።

ፋርስ ዜና ወኪል ከኻሜኒ ቀብር በኋላ የመሪው ማንነት ይፋ እንደሚደረግ እና የሹመት ሥነ ሥርዓቱም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሆን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ለአገራቸው ጠላት የሆነ የትኛውም ተተኪ ቢመጣ ዒላማቸው እንደሚሆን ተናግረዋል።

“እስራኤልን የማጥፋት ዕቅድን የሚቀጥል፣ አሜሪካን ላይ የሚዝት፣ የኢራንን ሕዝብ የሚጨቁን የትኛውም ተተኪ በማያጠራጥር ሁኔታ ለመደምሰስ ዒላማችን ይሆናል” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ።

አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የአገሪቱን ጠቅላይ መሪ ጨምሮ በርካታ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates