በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ ተብሎ በተጠቀሱት ቦታዎች ለብቻቸው ምርጫ እንዲደርግ መወሰኑ ተከትሎ የትግራይ ጊዝያዊ ኣስተዳደር ውሳኔውን ተቃወመ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/06/2018፡- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ፤ ሕገ ምንግሥቱን የሚጥስ እና የ ፕሪቶሪያውን ስምምነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲልም አስጠነቀቀ፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልል ውጭ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ምርጫ እንዲደረግ ያስተላለፈውን ውሳኔ በጽኑ የተቃወመው ሲሆን “በሕዝባችን ላይ ከተፈጸሙት ሊገለጹ የማይችሉ ግፎች እና የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ባሻገር፣ አሁን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱንም ሆነ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ የሚጻረር አዲስ ውሳኔ ተላልፏል” ብሏል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አምስት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልል ውጭ ሆነው ምርጫ እንዲያካሂዱ ወሰነ በሚል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ተከትሎ ነው ጊዝያዊ አስተዳደሩ እና ሌሎች የትግራይ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ተቃዉመዋቸውን እያሰሙ የሚገኙት፡፡
ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል ውጪ ሆኖው በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመርጡ ያላቸው አምስቱ የምርጫ ክልሎች የሑመራ፣ ዓዲ ረመፅ፣ ፀለምተት፣ ኦፍላ ኮረም እና ራያ አላማጣ ናቸው፡፡
ቦርዱ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን የምርጫ ክልል አወቃቀር መሠረት በማድረግ፣ በትግራይ ክልል ሆኖ ምርጫ እንደሚደርጉ ጥር 22 ቀን 2018 ዓ/ም አሳውቆ የነበረ ቢሆንም የፌደሬሽን ምክር ቤት ጥር 25 ቀን 2018 ዓ/ም ላከልኝ ባለው ውሳኔ መሰረት ትናንት የምርጫ ክልሎቹ ከትግራይ ውጭ እንዲሆኑ ይፋ አደርገዋል፡፡



