መካከለኛ ምስራቅዲፕሎማሲ
የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ እና የሳዑዲው ልዑል ሳልማን በዝግ መወያየታቸው ተገለፀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 17/06/2018፡- የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ሰኞ ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከሳዑዲው አልጋወራሽ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ሁለቱ ባለሥልጣናት በጋዛ፣ በቀጣናው ባለው ውጥረት እና በሌሎችም የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአልጋ ወራሹ የግል መኖሪያ ቤት በዝግ ውይይት ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
በአል ሲሲ ጉብኝት ሁለቱ አገራት የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉትን ምክክር እና ትብብር በማጠናከር የረጅም ጊዜ ግንኙነታቸውን ማስቀጠልን በተመለከተ መነጋገራቸው ተገልጿል።
ሁለቱ መሪዎች በቀጣናው ውጥረት እና ግጭት እንዳይኖር ለማድረግ፣ ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት፣ የአረብ አገራትን ትብብር ለማጠናከር እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ የአገራትን ሉዓላዊነት እንዲሁም የግዛት አንድነት ለማስከበር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።



