ቦርዱ አከራካሪ የሆኑ ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ የተላለፈውን ውሣኔ ይፋ አደረገ

ኢትዮ ሞኒተር፡ 16/06/2018፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው” በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ እንዳለው ያወጣውን የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ዝርዝር ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥር 25/2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ በሁለቱ ክልሎች መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ አምስት የምርጫ ክልሎች ጉዳይ እስኪፈታ ለብቻቸው ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።
እነዚህ በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ያቄ የተነሳባቸው እና ከሁለቱም ክልሎች ውጭ ሆነው በራሳቸው ምርጫ እንዲደረግባቸው የተወሰኑት የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምት እና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ናቸው።
በእነዚህ አምስት የምርጫ ክልሎች የሚገኙ መራጮች ድምጸቸውን የሚሰጡት ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ዕጩዎች ሲሆን፣ የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግሥት ውሳኔ ከተፈታ በኋላ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሳወቁን ቦርዱ ገልጿል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ ወር ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ጥር 22/2018 ዓ.ም. ምርጫ ክልሎች እና ምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።



