የተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ”ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው” አለ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 29/05/2018፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽነሩ ቮልከር ቱርክ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲናገሩ “በዚህ የተዛባ መረጃና ሳንሱር በሞላበት አለም እኛ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና ጭካኔዎችን የሚያጋልጥ ተአማኒና ወቅታዊ ሪፖርት የምናቀርብ ነን፡፡
እኛ ለተበደሉ፣ ለተጨቆኑና ለግፍ ለተጋለጡ ህዝቦች አጋር ነን” በማለት ገልፀዋል፡፡
በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለባለፈው አመት ማለትም ለ2025 የተመደበላቸው በጀት 246 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ነገር ግን ከዚህ ውስጥ የደረሳቸው 191 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
በተጨማሪም ከበጎ ፈቃደኞች የ500 ሚሊዮን ዶላር እገዛ መጠየቃቸውን ገልፀው ከዚህ ውስጥ እጃቸው የገባው 260 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለዘንድሮ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመስሪያ ቤታቸው የተመደበው በጀት 224.3 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ይሁንና በተመድ ውስጥ አሁን ካጋጠመው የገንዘብ ቀውስ በመነሳት ምን ያህሉ እንደሚሰጣቸው እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡
ጨምረውም ”አሁን በህልውና ስጋት ውስጥ እንገኛለን”፡፡
አሁን ኮሚሽኑ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው ከበጎ ፈቃደኞች ቢያንስ 400 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚገባው ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ የጠቀሱት ገንዘብ ካልተገኘ ህልውናቸው አስጊ እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡



