የአፍሪካ ሕብረት ሰሙኑን በትግራይ እየታየ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሳሰበው ገለፀ፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ተደራዳሪ አካላትን አቀራርቦ ለማወያየት ዝግጁ መሆኑም ሕብረቱ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/05/2018፡- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በትግራይ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ሁኔታውም ጥልቅ ስጋት እንደፈጠረባቸው አስታወቁ።
ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ፤ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የተገኘው ድል ተጠብቆ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ሊቀ መንበሩ ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመካከላቸው ያለውን መተማመን ሊሸረሽሩ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ማንኛቸውም ያልተቋጩ ጉዳዮች ካሉ በሰላም ስምምነቱ መንፈስ እና ግዴታዎች መሠረት ገንቢ በሆነ ውይይት እንዲፈቱም አሳስበዋል።
አፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ያለውን ጽኑ አቋም በድጋሚ ያረጋግጣል ያሉት ሊቀ መንበሩ ህብረቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሚካሄደው የሰላም ግንባታ እና የዕርቅ ሂደት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተቋቋመው የህብረቱ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ውይይት፣ ትብብር እና መተማመንን የማሳደግ ሥራ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑም አረጋግጠዋል።
ምንም እንኳን በትግራይ ይሁን በፌደራል መንግስት እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም በፀለምት አከባቢ በመከላከያ ሰራዊትና በትግራይ ሐይሎች መካከል ግጭቶች እንደተከሰቱ እየተገለፀ ይገኛል፡፡



