የአውሮፓ ህብረት በሱዳን ሰባት ግለ ሰዎችን በጥቁር መዝገብ ማስፈሩ ተገለፀ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጄነራል መሐመድ ዳጋሎ ወንድም ይገኙበታል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/05/2018፡- የአውሮፓ ህብረት አርብ ዕለት በሱዳን እየተባባሰ በመጣው ግጭት ምክንያት በሰባት ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፤ ይህም በመላ አገሪቱ ለተፈጸመው ጭካኔ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ምላሽ ለመስጠት ከሁለቱም ተዋጊ ቡድኖች እና ከተባባሪ ሚሊሻዎቻቸው የተውጣጡ አዛዦችን ኢላማ ያደረገ ነው ተብለዋል።
የንብረት እና የጉዞ እገዳን ጨምሮ እነዚህ የቁጥጥር እርምጃዎች በአውሮፓ ህብረት ከዚህ በፊት የሱዳን የማዕቀብ ማዕቀፍ ስር የተካተቱት ግለሰቦችን ጨምሮ አሁን ወደ 18 ያደርሰዋል።
በአውሮፓ ሕብረት ጥቁር መዝገብ ከተካተቱት መካከል አምስቱ ከፈጣን የድጋፍ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ፣ የብድኑ መሪ መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወንድም የሆኑት ሜጀር ጄነራል አልጎኒ ሃምዳን ዳጋሎ ሙሳ እንደሚገኙበት የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
እንዲሁም በቪድዮ እየቀረፀ ንፁሃን ዜጎችን ሲገድ ተይዞ ነገር ግን በኃላ የተለቀቀው የፈጣን ድጋፍ ሐይሉ አባል የሆነው አቡሉሉ” በመባል የሚታወቁት አል-ፋቲህ አብዱላህ ኢድሪስም በአውሮፓ ሕብረት ማዕቀብ ተደርጎበታል፡፡
ሌሎች ሁለት ከሱዳን የጦር ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ደግሞ የእስላማዊ ሚሊሻ ባራ ቢን ማሊክ ሻለቃ አዛዥ አል-ሚስባህ አቡ ዛይድ ታልሃ ይገኙበታል።
“የዚህ ጦርነት ኃላፊነት አሁንም በፈጣን የድጋፍ ኃይሎች እና በሱዳን የጦር ኃይሎች እንዲሁም በእነርሱ ተባባሪ ሚሊሻዎች ትከሻ ላይ ነው” ሲል ምክር ቤቱ ገልጾ፣ “በዳርፉር እና በመላ አገሪቱ በሰው ሕይወት ላይ የማይተካ ኪሳራ ያስከተለው ዓመፅ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠያቂዎች ናቸው” ሲል ጠቅሷል።
ማዕቀቡ የተጣለው ጥር 19 ቀን 2026 የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) ምክትል አቃቤ ህግ ካን ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ባደረጉት አጭር መግለጫ ተከትሎ ሲሆን፣ በተለይም በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የሰሜን ዳርፉር ከተማን ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የRSF ከበባ ወቅት በኤል ፋሸር የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።



