የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ሠራዊት አዛዥን አወገዘ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/05/2018፡- የደቡብ ሱዳን ሰራዊት አዛዥ “ማንንም እንዳትምሩ” በሚል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ የተባበሩት ድርጅት አውግዞታል።
የተባበሩት መንግሥታት አንድ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ “ህጻናት፣ አረጋውያን እና ንጹሃንን” ጨምሮ “ማንንም እንዳትምሩ” በሚል ያስተላለፉት ትዕዛዝ እጅጉን እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የደቡብ ሱዳን ሠራዊት ምክትል ዋና አዛዥ የሆኑት ጄነራል ጆንሰን ኦሉኒ፤ ይህንን ያሉት ወታደሮችን በታጣቂዎች ወደ ተያዙ አካባቢዎች እያሰማሩ በነበረበት ወቅት መሆኑ የተዘገበ ሲሆን “እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በሲቪሎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚቀሰቅስ ንግግር እጅግ አጸያፊ እና አሁኑኑ መቆም ያለበት ነው” ብለዋል ድርጅቱ።
በወታደራዊ አዛዡ ትዕዛዙ የተሰጣቸው ‘አግዌሌክ’ የተባሉት የሚሊሻ ኃይሎች ወደ ጆንግሌይ ግዛት ሲላኩ ይህን ትእዛዝ እንደተሰጣቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
ከሥልጣን የታገዱት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር አጋር የሆኑ ኃይሎች ባለፉት ሳምንታት በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።
ማቻር በአሁኑ ወቅት በነፍስ ግድያ፣ በአገር ክህደት እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የተመሰረተባቸው ክስ በመታየት ላይ ይገኛል። የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ግን የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች ውድቅ አድርገዋል።
የአገሪቱ ሠራዊት፤ በጆንግሌይ ግዛት በሚገኙ ሦስት አውራጃዎች ውስጥ በሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ላይ የሚያካሂደውን ጥቃት ከመክፈቱ አስቀድሞ ሁሉም ሲቪሎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች እና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ ይታወሳል።



