የታዳጊ አገራት የብድር ጫና ለዓለም ኢኮኖሚ ሥጋት ነው ሲል ዓለም ባንክ አስጠነቀቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 18/05/2018፡- የታዳጊ አገራት የብድር ጫና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ይህም ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መቃወስ ትልቅ ሥጋት መሆኑን የዓለም ባንክ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።
ባንኩ በፋይናንሻል ታይምስ በኩል ይፋ እንዳደረገው በርካታ ታዳጊ አገራት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸው (GDP) ጋር የማይመጣጠን ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ በመዘፈቃቸው መሠረታዊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወንና ዕዳቸውን ለመክፈል እየተቸገሩ ይገኛሉ።
ይህ የብድር ቀውስ በአፋጣኝ እልባት ካላገኘ በታዳጊ አገራት ላይ ብቻ ሳይወሰን በበለጸጉት አገራት የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ የማይቀር መሆኑ ተመልክቷል።
እንደ መግለጫው ከሆነ የወለድ መጠኖች መጨመርና የዓለም አቀፍ የንግድ መዳከም የታዳጊ አገራትን የመክፈል አቅም ይበልጥ አዳክሞታል።
ይህም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ድንገተኛ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል ባንኩ አመልክቷል። የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት እንደገለጹት አገራት የብድር ሽግሽግ (Debt Restructuring) ካልተደረገላቸውና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ካላገኙ ኢኮኖሚያቸው ለከፋ ውድቀት ሊጋለጥ ይችላል።
የዓለም ባንክ አክሎም ባለሀብቶችና አበዳሪ ተቋማት የታዳጊ አገራትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ አዳዲስ የብድር አከፋፈል ስልቶችን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በቅርቡ ያወጣው “Global Debt Monitor” የተሰኘ ጥናት እንደሚያመለክተው ፣ የታዳጊ አገራት አጠቃላይ የብድር መጠን ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
ጥናቱ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ከ60% በላይ የሚሆኑት ለከፍተኛ የብድር ሥጋት መጋለጣቸውን ያረጋግጣል።



