የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ዋሽንግተን እና ኒውዮርክ የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዙ አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 18/05/2018፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. እና በኒውዮርክ አካባቢ ባለው አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት ወደ አሜሪካ የሚደረጉና ከአሜሪካ የሚመለሱ በርካታ በረራዎችን መሰረዙን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ መሰረዙ ምክንያት ለተቸገሩ ተጓዦች እንደ አስፈላጊነቱ የበረራ ቦታን በመቀየር፣ የጉዞ ፕሮግራምን ዳግም በማስተካከል ወይም የከፈሉትን ገንዘብ ተመላሽ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በተጨማሪም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንና አዳዲስ መረጃዎች ሲኖሩ ወዲያውኑ እንደሚያሳውቅ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦች ለጉዞ ከመነሳታቸው በፊት የአየር መንገዱን ድረ-ገጽ፣ የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ወይም የዓለም አቀፍ ደንበኞች አገልግሎት ማዕከልን በማነጋገር የበረራቸውን ሁኔታ እንዲያረጋግጡ አሳስቧል።
እንዲሁም፣ በረራዎቹ የተሰረዙት የተጓዦችን እና የሰራተኞችን ደህንነት ከሁሉ በላይ ለማስቀደም ሲባል መሆኑንም አመልክቷል።
የተሰረዙት በረራዎች ET 500፡ ጥር 16 ቀን ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን፣ ET501፡ ጥር 17 ቀን ከዋሽንግተን ዲ.ሲ. ወደ አዲስ አበባ፣ ET 514፡ ጥር 17 ቀን ከአዲስ አበባ ወደ ኒው ዮርክ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ፣ ET 515፡ ጥር 17 ቀን ከኒው ዮርክ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎች ናቸው።



