ሶማሊያ አዲሱን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የመመስረቻ ስምምነት በይፋ አጸደቀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/05/2018፡- ረቡዕ ዕለት በሶማሊያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው ይህ ስምምነት፣ በቀጠናው የትብብር እና የውህደት ሂደት ላይ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ኢጋድ አስታውቋል።
ስምምነቱ ለምክር ቤቱ የቀረበው በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር ባልካድ ሲሆን፣ ህጉ ለሶማሊያ ቀጠናዊ ተሳትፎ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን በማስረዳት ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው ጠይቀው ነበር።
በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ሼክ አደን መሀመድ ኑር (ማዶቤ) በተመራው እና እጅ በማውጣት በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ፤ በዕለቱ ከተገኙ 144 የፓርላማ አባላት መካከል 141ዱ ስምምነቱን ሲደግፉ፣ ሁለት አባላት ተቃውመዋል፤ አንድ ድምፅ ደግሞ ታቅቧል።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የሶማሊያን ውሳኔ በደስታ ተቀብለውታል።
“ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የኢጋድን ስምምነት በማፅደቋ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፤ የሶማሊያ ፓርላማ እና መንግስት ለወሰዱት ወሳኝ አመራርም ምስጋና አቀርባለሁ” ሲሉ በመግለጫቸው አስፍረዋል።
ሶማሊያ ይህንን ስምምነት በማፅደቅ ከጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ በመቀጠል አምስተኛዋ ሀገር ሆናለች።
ይህም ኢጋድ 40ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ወቅት፣ የተሻሻለውን የህግ ማዕቀፍ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስፈልገውን የሁለት-ሦስተኛ አባል ሀገራት ድጋፍ እንዲያሟላ አስችሎታል።
ይህ አዲስ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ1996 ተፈርሞ የነበረውን የኢጋድ የመመስረቻ ስምምነት የሚተካ ነው።
የተሻሻለው የህግ ማዕቀፍ አባል ሀገራት በሰላምና ጸጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፣ በመሰረተ ልማት፣ በጤና፣ በንግድ እና በማህበራዊ ልማት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።



