የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሱዳንን ቀውስ እያባባሰች ነው በማለት ከሰሱ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/04/2018፡- ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ብቸኛ የቴሌቭዥን ጣቢያ ትላንት ምሽት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከአሜሪካ ስለጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ከግብፅ እና ሳውዲ አረቢያ ያላቸው ግንኙነት፣ ሰለ ቀይ ባህር እና የሱዳን ቀውስ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግስት ታወጀብን ስላሉት ጦርነት ማቤብራሪያ ሰጥቷል።
በሱዳን ውስጥ የነበረውን ስርዓት በህዝባዊ አመፅ ከተወገደ በኃላ የሽግግር መንግስት መቋቋሙን ያስታወሱት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሽግግር ምክር ቤቱ ወደ ሲቪላዊ አስተዳደር እንዲሸጋገር ነበር ዓላማው ብሏል።
“እኛ የሽግግር ምክር ቤቱ ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር የመምራቱን ሀሳብ ደግፈናል። በዚሁ መሰረት፣ በ2022 አንድ ሰነድ አዘጋጅተን ለሽግግር ምክር ቤቱ አቅርበን ነበር።
የጋራ መግባባቱ የሉዓላዊ ምክር ቤቱ በከፍተኛው የሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስልጣን እንደሚያስረክብ ነበር። ሆኖም፣ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ይህንን ሂደት አደናቀፉት” ብሏል።
የእነዚህ የውጭ አካላት ዋና ዓላማ የሱዳንን ቀውስ በመጠቀም ቀጠናውን ማተራመስ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዋነኛው አተራማሽ አካል ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት ሲሉ ከሷል።
“የሱዳን ቀውስ እንደ እርስ በርስ ጦርነት፣ ወይም በሁለት ጄኔራሎች መካከል ያለ ፉክክር ተደርጎ ብቻ ሊገለጽ አይችልም። እነዚህ ጊዜያዊ፣ ጊዜው የተገደበ፣ ባለአደራ ተቋማት ናቸው።
በዚህ እይታ፣ በሲቪል አስተዳደር ስር ለዘላቂ ሰላም መንገድ ለመክፈት የሽግግር ምክር ቤቱን መደገፍ ብቸኛው አዋጭ መፍትሄ ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ ለሱዳን መንግስት ያላቸውን ድጋፍ በይፋ አረጋግጧል።
“በተለያዩ አካላት (የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ ኳድ፣ ወዘተ) የሚነሱ ከእውነታው የራቁ ሀሳቦች እና የተለመዱ ንግግሮች፣ እንዲሁም የበዙ ተነሳሽነቶች ቀውሱን ከማራዘም እና ከማወሳሰብ ውጪ አይፈይዱም።
ግብፅ እና ሌሎች የቀጠናው ሀገራት በሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚና መጫወት አለባቸው” በማለትም ለግብፅ ጥሪ አቅርቧል።



