በቬኒዙዌላ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጠራ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡- 27/04/2018፡- አሜሪካ በቬኒዙዌላ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት በተመለከተ ለመወያየት የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጠራ፡፡ ስብሰባው እንዲጠራ ጥያቄ ያቀረበችው ኮሎምቢያ ስትሆን ጥያቄውን ቻይናና ሩሲያ ደግፈውታል፡፡
በጥያቄው መሰረት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ መያዙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካና በቬኒዙዌላ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የፀጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም(በኦክቶበርና በዲሴምበር) ሁለት ጊዜ ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአለማችን መሪዎች የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ድርጊቱን የመቃወምም ሆነ የመደገፍ አዝማሚያ ባያሳዩም በደፈናው ‹‹ሽግግሩ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና የቬኒዙዌላን ህዝብ ፍላጎት የሚያከብር መሆን አለበት›› ብለዋል፡፡
የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬደሪክ መርክ በበኩላቸው የአሜሪካ እርምጃ እጅግ ውስብስብ መሆኑን ገልፀው እርምጃውን ለመገምገም ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል፡፡
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ደግሞ ‹‹በእርግጥ ስፔን የማዱሮን አገዛዝ አትደግፍም፡፡
እንዲሁም አለም አቀፍ ህግን የሚጥስና ጠብ ጫሪነትን የሚያበረታታ ጣልቃ ገብነትም አትቀበልም›› ብለዋል፡፡
የተመድ ዋና ፀሀፊው አንቶኒዮ ጉተሬዥ እንዲህ አይነት ድርጊቶች አደገኛ ውጤት እንደሚኖራቸው ገልፀው አለም አቀፍ ህግ መከበር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ደግሞ ‹‹ፕሬዝደንት ትራምፕ እንኳን ደስ አለዎት፡፡
ለነፃነትና ፍትህ ሲሉ ላደረጉት ደፋርና ታሪካዊ አመራር አመሰግናለሁ›› ብለዋል፡፡



