ሶማሊላንድ፤ “ፍልስጤማውያንን ለማስፈር እና የእስራኤል የጦር ሰፈርን ለመመስረት አቅዳለች” በሚል በሶማሊያው ፕሬዝዳንት የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/04/2018፡- የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ “ከእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ለማግኘት ሲባል ፍልስጤማውያንን ለማስፈርና የእስራኤል የጦር ሰፈርን ለማስተናገድ ሶማሊላንድ ተስማምታለች” ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ ያቀረቡትን ክስ ከእውነት የራቀ ነው አሉ።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ቀደም ሲል፤ የሀገራቸውን የስለላ መረጃ ዋቢ አድርገው በመጥቀስ ሶማሊላንድ ከእስራኤል እውቅናን ለማግኘት በሶስት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መስማማቷን ለአልጃዚራ ተናግረው ነበር።
እነሱም “ፍልስጤማውያንን በግዛቷ ማስፈር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤ ዳርቻ ላይ የእስራኤል የጦር ሰፈር እንዲመሰረት መፍቀድ እና የአብርሃም ስምምነት ማዕቀፍ አባል መሆን ናቸው” ብለዋል።
በምላሹ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የቀረቡትን ክሶች ሀሰት መሆናቸውን በመጥቀስ ውድቅ አድርጓቸዋል።
“የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ መንግስት፤ ፍልስጤማውያንን ለማስፈር ወይም በሶማሊላንድ የጦር ሰፈር ለመመስረት ታቅዷል በሚል በሶማሊያ ፕሬዝዳንት የቀረበውን ሀሰተኛ ክስ አጥብቆ ውድቅ ያደርጋል” ሲል መግለጫው አስታውቋል።
የስማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ከአልጃዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ እስራኤል ቀድሞውኑ በሶማሊላንድ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴ እንዳላት የሚጠቁም መረጃ ሶማሊያ እጅ ላይ እንደነበረ ገልፀው ነበር።
በመሆኑም እስራኤል ለሶማሊላንድ የምትሰጠው እውቅና፣ በምስጢር ሲከናወን የነበረውን ግንኙነት ይፋዊና መደበኛ ማድረግ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።



