አል ሻባብ ሶማሊያውያን በእስራኤል ላይ ጠመንጃ እንዲያነሱ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 23/04/2018፡- ቴል-አቪቭ ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የነጻ አገርነት ዕውቅና በመቃወም እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል ሻብብ ሶማሊያውያን በእስራኤል ላይ ጠመንጃ እንዲያነሱ ጥሪ አቀረበ።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ባስተላለፈው በቪዲዮ በተቀረጸ መልዕክት ሶማሊያውያን አገራቸውን ከእስራኤል ለመከላከል ታጥቀው እንዲነሱ ጥሪ አስተላልፏል።
የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሼክ አሊ ሞሐሙድ ራጌ ወይም አሊ ዳሂር ባቀረበው ጥሪ የሶማሊላንድ መሪዎችን “ከሃዲ” በማለት በሶማሊያ ሕዝብ ላይ “ቅኝ ግዛትን ጋብዘዋል” ሲል ከስሷል።
“ማንኛውም የሠለጠነ እና መሳሪያ ያለው በተለይ ወጣቶች ካሉበት ቦታ ሆነው በእስራኤል ላይ ጦርነት መጀመር አለባቸው” በማለት አይሁዳውያንን ዒላማ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
መሳሪያም ሆነ ሥልጠና ለሌላቸው ደግሞ ቡድኑ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ እንዲቀላቀሉት ጥሪውን አስተላልፏል።
በበርካታ አገራት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከዓለም አቀፉ ቡድን አል ቃኢዳ ጋር ትስስር እንዳለው የሚነገርለት አል ሻባብ ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ የሶማሊያ እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ የሽብር ጥቃትን በመፈጸም ይታወቃል።
የሶማሊያ መንግሥትን ለመጣል የሚዋጋው ቡድኑ ከአገሩ መንግሥት ባሻገር አሜሪካንን ጨምሮ በአጎራባች አገራት የሽብር ቡድን ተብሎ እየታደነ ያለ ነው።



