አፍሪካ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሱዳን ኤል ፋሽር ባደረገው ጉብኝት ሰላማዊ ሰዎች “አደገኛ በሆነ ሁኔታ” ውስጥ እንደሚገኙ አረጋገጠ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 21/04/2018፡- በታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው የሱዳን ከተማ ኤል ፋሽር የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች፣ ያለ ውኃና የንጽህና አገልግሎት በረሃብ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ዴኒስ ብራውን ትናንት ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ኤልፋሽር ከ500 ቀናት ከበባ በኋላ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል እጅ የወደቀች ሲሆን፤ ባለፈው አርብ ደግሞ አንድ አነስ ያለ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ቡድን ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አጭር ጉብኝት ለማድረግ ችሏል ተብሏል።

ከተማዋ በታጣቂዎቹ እጅ በወደቀችበት ወቅት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ስቃይ እና ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ መጠነ-ሰፊ በደሎች እንደተፈጸሙ ተዘግቧል። ኤኤፍፒ የተመለከታቸው የሳተላይት ምስሎችም የጅምላ መቃብር የሚመስሉ ቦታዎችን ያሳያሉ።

ዴኒስ ብራውን ከተማዋን “የወንጀል ስፍራ” ሲሉ ገልፀው፤ ቢሯቸው ትኩረት የሚያደርገው በሕይወት ለተረፉት እርዳታ ማዳረስ ላይ እንደሚሆንና ምርመራው ደግሞ በሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች እንደሚከናወን ተናግረዋል።

አክለውም “ታሳሪዎች አሉ ብለን ብናምንም፤ እስካሁን ግን የትኛውንም ታሳሪ ማየት አልቻልንም” ብለዋል።

ከሰብዓዊ እርዳታ አንፃር ሲታይ ኤል-ፋሽር አሁንም ቢሆን የሱዳን “የመከራ ማዕከል” ሆና ቀጥላለች ያሉት አስተባባሪዋ፤ በአንድ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባት የነበረችው ይህቺ ከተማ አሁን በከፋ ረሃብ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።

አያይዘውም “ኤል-ፋሽር የቀድሞ ገጽታዋ የጠፋባትና ባዶዋን የቀረች ከተማ ሆናለች” ሲሉ ገልፀዋታል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates