ኢትዮጵያ
በትግራይ ከተፈናቃዮች ረሃብ ጋር ተያይዞ እየወጣ ለው መረጃ መሬት ላይ የሌለ ነው – የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

ኢትዮ ሞኒተር፡ 15/04/2018፡- በትግራይ ክልል ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በተመለከተ መገለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫውም መንግሥት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
በህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎችም ዓመቱን ሙሉ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ነው ኮሚሽኑ ያስገነዘበው፡፡
በዚህ መሰረትም ከመስከረም ጀምሮ እስከ ታሕሳስ 2018 ዓ.ም ድረስ የተሟላና ያልተቆራረጠ የምግብ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሷል፡፡
ኮሚሽኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚቀከተለው ቀርቧል፡፡
መንግሥት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎቻችንን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ ይገኛል።
ሆኖም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የሚገልጽ የተሳሳተና የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይሁኔታ የማይገልጽ ዘገባ ሆኖ አግኝተነዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍን በሚመለከት በመደበኛነት ዓመቱን በሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ ስርጭት ሳይቆራረጥ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በህጻጽ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያም የሚገኙ ዜጎቻችን አመቱን ሙሉ ተመሳሳይ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበረ ሲሆን ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር 2018 ድረስ የተሟላና ያልተቆራረጠ የምግብ ስብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን መረጃዎችን ያሳያሉ።
በአሰገደ ወረዳ ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ባለፉት አራት ወራት የተደረገውን ድጋፍ በቁጥር ለመግለጽ ለ14 ሺህ 413 ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በተጨማሪም ከአጎራባች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ በመስከረም ወር 16 ሺህ 775 በጥቅምት ወር 18 ሺህ 290 በህዳር ወር 17 ሺህ 813 እንዲሁም በታህሳስ ወር የሚያስፈልገው ለ14 ሺህ 413 ዜጎች የሚያስፈልግ ምግብ ተሰራጭቷል።
በዚህም በድምሩ 11 ሺህ 406 ኩንታል ምግብ (ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬና የምግብ ዘይት) ባለፉት አራት ወራት እንዲዳርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይህ ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ257 ሚሊየን ብር በላይ ይሆናል።
በሌላ በኩል በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ችግሮች መኖራቸውንና ተጨማሪ የፌዴራል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢጠየቅ ኖሮ በኮሚሽናችን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለመፈጸም የሚያስችል ዝግጁነት ያለን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለተፈናቃይ ማሕበረሰብ የሚላከው ድጋፍ ለታለመለት አላማ ብቻ መዋሉን የማረጋገጥና ክፍተቶች ቢኖሩም እንዲሟላ የማድረግ ሃላፊነት የክልሉና የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን



