በሱዳን በፈጣን ድጋፍ ሓይል ቁጥጥር ስር በምትገኘው ኒያላ የጤና ባለሙያዎቼ ታስሪብኛል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዓመት በሱዳን በጤና እንክብካቤ ላይ 65 ጥቃቶችን መመዝገቡ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 08/04/2018፡- የዓለም ጤና ድርጅት በደቡብ ምዕራብ ሱዳን በኒያላ ከ70 በላይ የጤና ባለሙያዎች እና ወደ 5,000 የሚጠጉ ሲቪሎች የታሰሩ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡
“በሱዳን ደቡብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ከሆነችው ከኒያላ ከ70 በላይ የጤና ባለሞያ ሠራተኞች 5,000 ገደማ ሲቪሎች በግድ እየታሰሩ መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎች አሳስበናል” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ትላንት አስታውቀዋል።
“እንደ ሱዳን ዶክተሮች ኔትወርክ ገለጻ፣ ሰዎቹ በተጨናነቁ እና ጤናማ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የታሰሩ ሲሆን የበሽታ ወረርሽኝ እንዳጋጠማቸው የሚያሳዩ ሪፖርቶችም አሉ” ብለዋል።
የፈጣን የድጋፍ ኃይሎች እና የሱዳን ህዝባዊ ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን አንጃ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በኒያላ ትይዩ መንግስት መመስረታቸው ይታወሳል።
“የዓለም ጤና ድርጅት በእስር ላይ ስለነበሩት ሰዎች ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ እየሰበሰበ ነው፤ ሁኔታው በተባባሰ የጸጥታ ችግር የተወሳሰበ ነው” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል።
“የጤና ባለሙያዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች መታሰር በጣም ያሳስበናል” ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ “የጤና ባለሙያዎች እና ሲቪሎች በማንኛውም ጊዜ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፣ እናም ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዓመት በሱዳን በጤና እንክብካቤ ላይ 65 ጥቃቶችን መመዝገቡ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም 1,620 ሰዎችን ለሞት እና 276 ሰዎች ጉዳት አስከትሏል።
ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ 54ቱ የተጎዱ ሰራተኞች፣ 46 የተጎዱ ተቋማት እና 33 የተጎዱ ታካሚዎች ይገኙበታል።



