ኢትዮጵያ
20ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ተክብሯል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 20/03/2018፡- 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓል በዛሬው ዕለት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የተከበረ ሲሆን፣ በበዓሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአባቶቻችን ደም የወረስነውን ነጻነት በብልጽግና ማጽናት ከትውልዱ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ በሁሉም መመዘኛ ከጨለማ ወደ ንጋት እየተሸጋገረች መሆኑን ገልጸው፤ የወረስነውን ነጻነት ብቻ ሳይሆን የተሸከምነውን የትውልድ አደራ ማሰብ ይኖርብናል ብለዋል።
ብልጽግናን ማሳካት ፈታኝ ሂደት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ችግሯን ብቻ ሳይሆን አቅሟን ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የጸደቀበትን ህዳር 29 ቀን ለማስታወስ ነው።



