ጤና
የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 26/03/2018፡- የማርበርግ ቫይረስ ምላሽን ለማሳደግ የሚረዳ የሙከራ ክትባት ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ሊሰጥ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ክትባቱ ከሕዳር 29 ቀን ጀምሮ መስጠት የሚጀመር ሲሆን የጤና ባለሙያዎችን እና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ቡድኖች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።
ለዚህም የማርበርግ ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ 2 ሺ 500 የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት ከአሜሪካ መንግስት በድጋፍ የተገኘ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ክትባቱ በአርማወር ሃንሰን የምርምር ተቋም በሚመራ ፈጣን የደረጃ 2 ክሊኒካዊ ሙከራ ተደርጎለት ጥቅም ላይ እንደሚውልም ነው የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የገለጹት።
ጤና ሚኒስቴር ወርሽኙን ለመግታት ከሚመለከታችዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የምላሽ አሰጣጡን አጠናክሮ የቀጠሉ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ፤ ለዚህም የቅኝትና ቁጥጥር ስራዉን ማጠናከር፣ የጤና ባለሙያዉንና ጤና ሰራተኞች ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑትን በመጠበቅ ላይ ትኩረት በማድረግ የመከላከል ስራው አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አመልከተዋል።



