ፖለቲካ

ግብፅን የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ በአሁኑ በ21ኛው ክ/ዘመን ለመተግበር መሞከሯ ተቀባይነት እንደሌሎው ኢትዮጵያ ገለፀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/03/2018፡- በአፍሪካ ቀንድ “ተላላኪ፣ ደካማ እና የተከፋፈሉ ጥገኛ መንግስታትን” ለመፍጠር ያላትን ፍላጎት ኢትዮጵያ በፅኑ እንደምትቃወምም አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ረቡዕ ህዳር 24/2018 ዓ.ም ባወጣው ጠንከር ያለ መግለጫ፣ ከፍተኛ የግብፅ ባለሥልጣናት በአባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ፀብ አጫሪ ንግግራቸውን እያባባሱ ነው በማለት ከሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርብ ጊዜያት ከካይሮ በኩል የተሰጡ አስተያየቶችን “የግብፅ መንግሥት የ21ኛውን ክፍለ ዘመን እውነታዎች ለመቀበል ያለመቻሉ መገለጫዎች ናቸው” ብሏል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው፣ አንዳንድ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አሁንም “በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ውስጥ የተዘፈቁ” መሆናቸውን እንዲሁም በአባይ ወንዝ ላይ “የብቸኛ ባለቤትነት ወይም የጠቅላይነት አመለካከት አላቸው” ሲል በፅኑ ኮንኗል።

ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በተደጋጋሚ ማንሳቷን አጥብቆ የተቸ ሚኒስቴሩ፤ አዲስ አበባ “ካይሮ ለመተው እየከበዳት ያሉትን የቅኝ ግዛት ቅሪቶችን የምትሸከምበት ጫንቃም ሆነ የምታስተናግድበት ምንም ቦታ የላትም” ሲል አስጠንቅቋል።

“እነሱ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በመጥቀስ ስለ ‘ታሪካዊ መብቶቻቸው’ ያወሳሉ” ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ “ይህ የተሳሳተ አካሄድ እና ጥረት የአስተሳሰብ እና አመራር ውድቀት ነው። ኢትዮጵያን በፍጹም የማያስበረግጋትን ይህን የጃጀ የጨዋታ መመሪያ እና መርህ ለመተው ጊዜው አሁን ነው” ሲል አፅንኦት ሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ በተጨማሪም ግብፅ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጥረት ማድረጓን በመጥቀስ የወቀሰ ሲሆን፤ አያይዞም የግብፅ ባለሥልጣናት “ተላላኪ፣ ደካማ እና የተከፋፈሉ ጥገኛ መንግስታት”ን ለማስፈን በማሰብ “በኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ብቻ ያልተገደበ ቀጠናውን የማተራመስ ዘመቻ” ታካሄዳለች ሲል ከሷል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates