ዲፕሎማሲ
ሩሲያ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የምትገነባው ዘመናዊ በሆነውና ደህንነቱ በተጠበቀው VVER-1200 ቴክኖሎጂ መሆኑን ገለፀች::

ኢትዮ ሞኒር፡ 13/02/2018፡- የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) ዘመናዊ በሆነው እንዲሁም ደህንነቱ በተጠበቀው VVER-1200 ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደሚገነባ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን አስታወቁ።
በሩሲያ እና በኢትዮጵያ መካከል በትብብር የሚሰራ ለሰላማዊ አላማ የሚውል የኑክሌር ኃይል መስክ “የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ አጋርነትን ቀዳሚው መስክ” ሊያደርግ እንደሚችል አምባሳደሩ መግለፃቸውን የሩሲያ ዜና አገልግሎት (TASS) ዘግቧል።
በተያያዘ ዜና የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ ሀገራቸው በኃይል፣ በንግድ እና በዲፕሎማሲ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠው፣ በወታደራዊ ትብብር መስክም ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች ለማክበር ሞስኮ አሁንም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር በተወያዩበት መድረክ ነው። በውይይታቸውም ወቅት ሁለቱ ወገኖች በወታደራዊ-ቴክኒክ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን ግምገማ ማድረጋቸው ተዘግቧል።