“ሩሲያ 78 በመቶ የዩክሬን መሬት ተቆጣጥራለች” ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ፡፡
ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ነገሮች አሁን ባሉበት እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 11/02/2018፡- የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ 78 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን መሬት መቆጣጠሯን ገምተዋል ሲል አልጄዚራ ዘግበዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት፣ “ሁለቱም ወገኖች መዋጋት አቁመው ለወደፊት በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ወደ መፍትሄ መሄድ አለባቸው” ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ “እኔ የምለው አሁን ጦርነትን ማቆም፣ ወደ ቤታቸው መሄድ፣ ሰዎችን መግደል ማቆም አለባቸው። ያለበለዚያ የመጨረሻውን መፍትሄ በዝርዝር ለመወያየት አስቸጋሪ ይሆናል” ብለዋል።
የጦርነቱ አብዛኛው ክፍል የተካሄደበትን ዶንባስን በተመለከተ ምን ይሆናል ተብለው ሲጠየቁ ትራምፕ፣ “አሁን ባለበት ሁኔታ ጦርነቱ ይቁም ። እኔ እንደማስበው 78 በመቶ የሚሆነው መሬት በሩሲያ ተይዟል። አሁን ባለበት ይተውት። በኋላ ላይ መወያየት ይችላሉ” ሲሉ መልሰዋል።
ዩክሬን ከዚህ ቀደም መላውን መሬቷን መልሳ እንደምትወስድ አጥብቃ ስትናገር ቆይታለች። ትራምፕ እራሳቸው ባለፈው ወር ዩክሬን በጦር ኃይል ማሸነፍ እንደምትችል እና በሩሲያ የተያዘውን መሬት በሙሉ፣ የክራይሚያን ልሳነ ምድር እና ሌሎች የምስራቅ ዩክሬን አካባቢዎችን ጨምሮ መልሳ መውሰድ እንደምትችል ተናግረው ነበር።
ትራምፕ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሃንጋሪ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል፣ ነገር ግን ትክክለኛው የስብሰባው ቀን አልተገለጸም።