ማህበራዊ
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን ለመርዳት ትብብሩን እንዲያጠናክር ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 29/01/2018፡- ኢትዮጵያ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ባለው 76ተኛው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች መሆኑ ተገልጿል።
በስብሰባው የተገኙት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን ኢትዮጵያ ከ1.1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች እንደምትገኝ አስረድቷል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በርካታ ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በተለይም ያለፉት አስር አመታት ለሀገሪቱ እጅግ ፈታኝ እንደነበሩ አብራርተዋል።
አክለውም ከደቡብ ሱዳን የሚገቡ አዳዲስ ስደተኞች ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሳያገኙ መምጣታቸው የዘንድሮውን አመት ለኢትዮጵያ ፈታኝ እንዳደረገው አመላክተዋል ።
“የሠብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች እየጨመሩ ቢመጡም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፉ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱን” የጠቆሙት ወ/ሮ ጠይባ፤ ስደተኞችን ለመርዳት ከለጋሾች የሚገኘው ድጋፍ ስደተኞችን በበቂ ሁኔታ ለመርዳት ከሚያስፈልገው አንጻር አለመመጣጠኑ የተመዘገቡ ስኬቶችን አደጋ ላይ እየጣለ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብም ስደተኞችን ለመርዳት ትብብሩን እንዲያጠናክር እና ፍትሐዊ የሆነ የኃላፊነት ክፍፍል እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።