
ኢትዮ ሞኒተር፡ 28/01/2018፡- በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ እና ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በሆኑ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በወጪ መጋራት (ስኮላርሽፕ) ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች የተቋም ምደባ ይፋ መደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።
ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ በዌብሳይት እና በቴሌግራም ቦት ምደባቸውን ማየት እንደሚችሉ ገልጿል።
እንዲሁም የሪሚዲያል መግቢያ ነጥብ 33 በመቶ ሆኖ መወሰኑን ገልጿል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጥሮ እና ማሕበራዊ ሳይንስ ትምህርት መስኮች ከ49.5 በመቶ በታች ያስመዘገቡ ነገር ግን እንደተፈተኑት የትምህርት ዓይነት ብዛት በሁሉም አማራጮች (በግል እና በመንግሥት ተቋማት) ሪሚዲያል መርሃ ግብር ለመከታተል 33 መቶ እና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት ተቋማት ወጪያቸው በመንግስት ተሸፍኖ የሪሚዲያል ፕሮግራም የሚከታተሉ ተማሪዎች የመቁረጫ ነጥቡን ያሟሉ ብቻ መሆናቸውንም ሚንስቴሩ አስታውቋል።
በዚህም የተፈጥሮ እና የማሕበራዊ ሳይንስ ወንድ ተማሪዎች፤ 216 እና ከዚያ በላይ ያመጡ፣ የተፈጥሮ እና የማሕበራዊ ሳይንስ ሴት ተማሪዎች 204 እና ከዚያ በላይ ያመጡ፣ ታዳጊ ክልልና አርብቶ አደር አካባቢዎች የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በሁለቱም ፆታ 198 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ናቸው ተብሏል።
እንዲሁም የማሕበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች ለሁለቱም ፆታ 198፣ ማሐበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ለሁለቱም ፆታ 165 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ የሪሚዲያል መርሃ ግብሩን መከታተል የሚችሉ መሆኑን ሚንስቴሩ አስታውቋል፡፡