
ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/01/2018፡- በፍልስጤም ጋዛ ሰርጥ ውስጥ የተኩስ አቁም ለማድረግ ታስቦ በሃማስ እና በአስታራቂዎች መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ንግግር “በአዎንታዊ መልኩ” መጠናቀቁ ተገልጿል፤ ይሁን እንጂ በድርድሩ ሂደት ወይም ሊደረስበት በሚችል ስምምነት ላይ እስካሁን ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
እነዚህ ንግግሮች የጋዛ ጦርነትን ለማቆም እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንደገና እንዲቀጥል መንገድ ለመክፈት እንደ ዋና እርምጃ እየታዩ ነው።
የሃማስ ተወካዮች ሰኞ ዕለት በግብፅ ሸርም ኤል-ሼክ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
ከግብፅ፣ ከኳታር እና ከአሜሪካ የተውጣጡ ተወካዮች በአስታራቂነት ተገኝቷል።
የግብፅ መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አል-ቃሂራ ኒውስን እንደዘገበው፣ የመጀመርያው ቀን ስብሰባዎች የተካሄዱት በገንቢ መንፈስ ነው። ሆኖም በድርድሩ ሊደረስበት በሚችል ስምምነት ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አልተገኘም ብሏል።
የንግግሮቹ ዋና ግብ እስረኞችን እና ታጋቾችን የመለዋወጥ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ነው።
በሚጠበቀው ስምምነት መሠረት፣ በጋዛ የሚገኙ ሁሉም የእስራኤል ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ በምላሹ ደግሞ እስራኤል በእስር ቤቶቿ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ፍልስጤማውያንን ትለቅቃለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃማስ ለጋዛ የተኩስ አቁም ባቀረቡት ዕቅድ ውስጥ አንዳንድ አስፈላጊ ነጥቦችን እንደተቀበለ ገልጸዋል። ትራምፕ ሰኞ ዕለት በቢራቸው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ሃማስ አንዳንድ አስፈላጊ ነጥቦች ላይ ተስማምቷል ብሏል። ጥሩ መሻሻል እያመጣን ነው” ሲሉም ተደምጧል።
ይህ በእንዲህ እያለ በሁለት አመቱ የጋዛ ጦርነት የሟቾች ቁጥር 67,000፣ የተጎጂዎች ደግሞ 170,000 መድረሱ ተገልጿል።