ታዋቂዎቹን የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ ባንኮች ስታንዳርድ ቻርተርድ እና በርክሌይን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የውጭ ባንኮች ከአፍሪካ እየወጡ መሆናቸውን ጥናት አመላከተ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 23/01/2018፡- ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሰቨን የዓለም የንግድ ማዕከል ያደረገውና ከተመሰረተ 116 ዓመታትን ያስቆጠረው የሀገራትንና የኩባንያዎችን እዳና ብድር በመለካት ዓለም አቀፉ “ሙዲስ/Moody’s/” ኩባንያ አዲስ ባወጣው ሪፖርት ዓለም አቀፍ የውጭ ባንኮች ከሀገረ ከአፍሪካ እየወጡ መሆናቸውን አመላክቷል።
በአህጉሪቱ የአገር ውስጥ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማትና አዳዲስ ዲጂታል ተገዳዳሪዎች ዘርፉን በበላይነት መቆጣጠራቸው ለውጭ ባንኮች ከአፍሪካ መውጣት ዋነኛው መንስኤ መሆኑን የጥናቱ ሪፖርት ገልጿል።
በዚህም የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተዋናዮችና ሞባይል ባንኪንግንና ሌሎችንም ዲጂታል ባንኪንግ ዘዴዎች በመጠቀም በከፍተኛ ደረጃ ለሕብረተሰባቸው ብድርና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ አዳዲስ የቴክኖ-ፋይናንስ ድርጅቶች ቀድመው በዘርፉ ጠንካራ መሠረት በመያዛቸው የተነሳ ዓለም አቀፍ የውጭ ባንኮች በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም የአፍሪካ ክፍሎች የብድር አገልግሎቶችን በመስጠት ትርፋማ ለመሆን እየተቸገሩ መጥተዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በአህጉሪቱ አሁንም ድረስ መሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለመስፋፋት፣ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ የማንነት መለያ ሥርዓት አለመዘርጋትና መሰል መዋቅራዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውና ይህም በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ማነቆ መሆኑ ለውጭ ባንኮቹ ከአፍሪካ መውጣት በተጨማሪ መንስኤነት ቀርበዋል።