
ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/01/2018፡- ኢትዮጵያ በ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የግብጽ ተወካይ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ኢትዮጵያን አስመልክቶ ላቀረቡት የሐሰት ክስ ምላሽ ሰጥታለች።
በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በኒውዮርክ በተካሄደው 80ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ‘እኔ ብቻ ልጠቀም’ የሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን ታሪክ በማድረግ በተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብት ትብብር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት መርህ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።
አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በጠቅላላ ጉባኤው የሥነ ስርዓት ደንብ ላይ የተቀመጠውን ምላሽ የመስጠት መብት ተጠቅመው፤ ግብጽ ላነሳችው ሀሳብ መልስ ሰጥተዋል።
የግብጽ ተወካይ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ የአባይ ውሃን ለመጠቀም እየመኮረች ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ግን ግብፅ አዲስ ክስ ይዛ ብቅ ብላለች። “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እየሰራች ነው” የሚል።
የግብፅ ተወካይ በኢትዮጵያ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎም፤ ኢትዮጵያ የሁለተኛ ምላሽ መብቷን ተጠቅማ በአምባሳደር ዮሴፍ አማካኝነት በድጋሚ መልስ የሰጠች ስትሆን የናይል ወንዝ የተፋሰሱን ሀገራት ለዘመናት ያቆራኘ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህን ትስስር ለማጥበቅ ስትሰራ መቆየቷን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለረጅም ጊዜ ትብብር ያማከለ አካሄድን ስትከተል መቆየቷን የጠቆሙም ሲሆን፤ በተቃራኒው ግብፅ ‘ታሪካዊ መብት አለኝ፣ እኔ ብቻ ልጠቀም’ የሚል ጊዜው ያለፈበት የቅኝ ግዛት እሳቤ እያራመደች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲተገበር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በአንጻሩ ግብጽ የሁለትዮሽ የቅኝ ግዛት ስምምነትን ለማስቀጠል በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ተገቢነት የሌለው ጫና እያሳደረች መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር በተፈራረመችው የመርሆዎች ስምምነት አማካኝነት የግድቡን ሙሌት እና ሥራ አስመልክቶ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ መረጃ ተደራሽ ስታደርግ መቆየቷን አብራርተዋል።
በሦስትዮሽ ድርድሩም ኢትዮጵያ ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ መንገድን ብትከተልም፤ ግብጽ ድርድሩን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችን ስትፈጽም መቆየቷን ተናግረዋል።
ግብጽ በድርድሩ ወቅት ‘የውሃ ባለቤትነትና ድርሻ ላይ ስምምነት መደረስ አለበት’ በሚል ስታራምድ የነበረው ግትር አቋም ስምምነት እንዳይደረስ መሰናክል መፍጠሩንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የግብጽን የቅኝ ግዛት ትርክትና ‘እኔ ብቻ ልጠቀም’ የሚል አባዜ ፈጽሞ አትቀበለውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከርና ሽብርተኝነትን በመከላከል የጋራ ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ በቀጣናው ገንቢ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም ገልጸዋል።
ግብጽ ክፍፍልን የሚፈጥሩ፣ ሀብትን የሚያባክኑና በጋራ መልማትን የሚያሰናክሉ አካሄዶችን እየተከተለች ትገኛለች ሲሉም አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ አስታውቀዋል።
በቀጣናው ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች መሳሪያ በመስጠት አሉታዊ ተግባር እየፈጸመች መሆኑን አክለዋል።
የሁለቱም አገሮች በዓለም ማህበረሰብ ፊት የገቡት እሰጣገባ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚል የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።