የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአገራቸው ውስጥ እንዲዋጉ እንደማይፈቅዱ ተናገሩ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/01/2018፡- የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአገራቸው በሰላም ማስከበር ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮች ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ “የውክልና ጦርነት” አይኖርም አሉ።
ፐሬዝዳንቱ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል “በሶማሊያ ምድር” የሚካሄድ ጦርነት እንደማይኖር እና ሶማሊያም ይህንን እንደማትፈቅድ አሳውቀዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በሶማሊያ ውስጥ ግጭት ውስጥ ሊገቡበት የሚችሉበት ዕድል እንደሌለም ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባት የሚፈልጉ ከሆነ በራሳቸው ሊዋጉ ይችላሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ነገር ግን በሶማሊያ ምድር የሁለቱ አገራት ሠራዊት የሰፈሩት ቦታ ተቀራራቢ ስላልሆነ” ለግጭት የሚያበቃ ዕድል የለም ብለዋል።
በግብፅ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት መኖሩን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ “ግብፅ ኢትዮጵያን ለመረበሽ የምትፈልግበት ምክንያት አይታየኝም። ኢትዮጵያም በሶማሊያ የሚገኙ የግብፅ ሰላም አስከባሪ ኃይልን ለመረበሽ የምትፈልግበት ምክንያት አይታየኝም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮች ሶማሊያን የጦርነት አውድማ የሚያደረግ “የውክልና ጦርነት” ማድረግ እንደማይቻል ሶማሊያም ይህ በግዛቷ እንዲከናወን እንደማትፈቅድ አሳውቀዋል።