
ኢትዮ ሞኒተር፡ 13/01/2018፡- ግብፆች በዓባይ ጉዳይ የዓለም ሀገራትን ከጎናቸው ለማሰለፍ እና በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ 560 ስብሰባዎችን አካሂደው እንደነበር ተገለፀ
ግብፆች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የዓለም ሀገራትን ከጎናቸው ለማሰለፍ እና በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ 560 ስብሰባዎችን አካሂደው እንደነበር በዓባይ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ሲሟገቱ የሚታወቁት የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ። ግብፅ ግድቡን ለመምታት ራፋል የተባለ የጦር አውሮፕላን ገዝታ እንደነበርም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
ከበኩር ጋዜጣ የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም እትም እንግዳ አምድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ምሁሩና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል፤ “ከጥንት ጀምሮ የግብፅ መሪዎች ኢትዮጵያ ጠንካራ እንዳትሆን እንዲሁም አንድነት እንዳይኖራት ያላደረጉት ጥረት ያልፈፀሙትም ሴራ የለም” ብለዋል።
በተለይም ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ከገማል አብደላ ናስር እስከ አንዋር ሳዳት፣ ከሙሀመድ ሙርሲ እስከ አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ “ኢትዮጵያን እናጠፋለን” የሚል ዛቻ እስከመሰንዘር የደረሰ እንደነበር አመላክተዋል።