ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ስለ ሕዳሴ ግድብ ያስገባችውን ክስ በተመለከተ ኢትዮጵያ ለምክር ቤቱ በቂ የጽሑፍ ማብራሪያ አስገብታለች ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 08/01/2018፡- ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ስለሕዳሴ ግድብ ያስገባችውን ክስ በተመለከተ ኢትዮጵያ ለምክር ቤቱ በቂ የጽሑፍ ማብራሪያ አስገብታለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዛሬ መስከረም 8/2018 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፣ “የሕዳሴ ግድብ መመረቅ ኢ-ፍትሐዊ የነበረውን የውኃ አጠቃቀም ትርክት ቀይሮታል” ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክቱ የዓባይ ውኃን አጠቃቀም ወደ ፍትሐዊ አቅጣጫ የቀየረ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ አክለውም ግድቡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም በመጨመር ተደማጭነትን የሚያሳድግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ስለሕዳሴ ግድብ ያስገባችውን ክስ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቃል አቀባዩ “ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲከበር እና ፍትሐዊ የመልማት ፍላጎት ብቻ እንዳላት” አፅንኦት ሰጥተዋል።
አያይዘውም “የኢትዮጵያ ጥያቄ እና ፍላጎት ተገቢ ስለመኾኑም ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በቂ የጽሑፍ ማብራሪያ አስገብተናል” ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የባሕር በርን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም “ኢትዮጵያ ሰላማዊ በኾነ መልኩ ነው የባሕር በር ጥያቄ እያቀረበች ያለችው፤ የባሕር በር ጥያቄ ለምን እንደሚያስፈልጋት የምናውቀው እኛ እንጂ ከውጭ ምላሽ የሚሰጡ አካላት አይደሉም” ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በዚህም “ብዙ ወዳጆች የኢትዮጵያ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን እያመኑበት ነው” ሲሉ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤና በአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ጉባኤዎች ላይ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኗን ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣይ በሚካሄደው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ “ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳለች” ስትል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ አቤቱታ ማሰማቷ አይዘነጋም።
በደብዳቤው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የህዳሴው ግድብ ምርቃት “በሕግ ሊደገፍ የማይችል ሕገወጥ የአንድ ወገን ተግባር” ነው ብለዋል።
አያይዞም “ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የህልውና ጥቅም በቀላሉ ትተዋለች ማለት ከንቱ ምኞት ነው” ሲል ገልጾ፣ “ኢትዮጵያ የጋራ በሆነው የውሃ ሃብት ላይ በብቸኝነት ቁጥጥር እንድታደርግ ግብጽ አትፈቅድም” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
ካይሮ የህልውና ጥቅሟን ለማስከበር እንዲሁም በአለም አቀፍ ህግ እና በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ስር የተፈቀዱትን ማናቸውም እርምጃዎች ለመውሰድ እንደምትችል ገልጻለች።